ቀጥታ፡

ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የኢትዮጵያ ብዝኃነት ማሳያ ናቸው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፦ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የኢትዮጵያ ብዝኃነት ማሳያ መሆናቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የመስቀል ደመራ በዓል ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወራረሰ እና ተጠብቆ የቀጠለ ክዋኔን የሚያሳይ የኢትዮጵያ ብዝኃነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ ነው ብሏል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበዉም ይህንን ነባር የአከባበር ትውፊቱን ይዞ እንዲቀጥል፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የሰው ልጆች ኹሉ የጋራ ቅርስነቱ እንዲጠበቅ ለማስቻል ነው፡፡

ኢትዮጵያውያንም የመስቀል ደመራ በዓልን በየዓመቱ ጥንታዊነቱንና ማኅበራዊ እሴቱን ጠብቀዉ ያከብሩታል፡፡ መንግሥት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸዉ የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ለኾነው የቱሪዝም ዕድገትም የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጿል።

የዘንድሮውን የመስቀል ደመራ በዓል የምናከብረው ደግሞ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳካነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድልን እያከበርን ባለንበት ወቅት መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህም በዓሉን የበለጠ ደማቅ ያደርገዋል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም