በብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል የሴቶች ክንፍ በኢሉባቦር ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አከናወኑ - ኢዜአ አማርኛ
በብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል የሴቶች ክንፍ በኢሉባቦር ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አከናወኑ
መቱ ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፦ ''በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ በብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል የሴቶች ክንፍ በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አከናወኑ።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የቤት ግንባታ ቁሳቁሶች፣ የትምህርት መሳሪያዎችና የንጽሕና መጠበቂያን ጨምሮ ሌሎችም ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል።
በዚሁ ወቅት በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል የሴቶች ክንፍ ኃላፊ ወይዘሮ መዓዛ ተስፋዬ፤ አብሮነታችንን ማጠናከር ለሁለንተናዊ ብልጽግና እውን መሆንና ለጋራ ተጠቃሚነታችንም መረጋገጥ ትልቅ መሠረት ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል በጋምቤላ ክልል የትምህርት ቤት ግንባታ በማከናወን አብሮነት ይበልጥ እንዲጠናከር መደገፉን አስታውሰዋል።
ይህም ለሀገር ግንባታ እና ከፍታ መሠረት መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያከናወኑት ተግባርም ለወደፊት አብሮነትን ይበልጥ ማጠናከሪያ የሚሆን ነው ብለዋል።
በተለይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከጋምቤላ ክልል ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የኢሉአባቦር ዞን ጋር ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እንዲጠናከር ያግዛል ነው ያሉት።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል የሴቶች ክንፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሳሚያ አብደላ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሁለቱ ክልሎች ማሕበረሰቦችን ትስስር ይበልጥ የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በኩል የሚተገበር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንድነትንና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደመር እሳቤ ማሳያና የኢትዮጵያ ከፍታ ማረጋገጫ አንዱ መሳሪያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው፤ በተጎራባቾቹ የጋምቤላ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የኢሉባቦር ዞን ጠንካራ ትስስር መኖሩን ገልጸዋል።
ዛሬ የተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከቁሳቁስ ድጋፍ ያለፈ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ባሕል፣ ወግና እሴት እንዲሁም የአንድነት ማጠናከሪያ ትልቅ መሳሪያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።