ኢትዮጵያ እና ቻይና በብሪክስ ማህበረሰብ መካከል ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት ለማሳደግ በትብብር እየሰሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቻይና በብሪክስ ማህበረሰብ መካከል ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት ለማሳደግ በትብብር እየሰሩ ነው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ቻይና በብሪክስ ማህበረሰብ መካከል ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት ለማሳደግ በትብብር እየሰሩ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ ስምምነት በኢትዮጵያና ቻይና የግል ካምፓኒዎች መካከል የኢንዱስትሪ ትብብር ተፈርሟል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ቻይና በኢኮኖሚ ትብብር፣ በህዝብ ለህዝብ እና የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች ላይ ዓመታትን የተሻገረ አጋርነት አላቸው፡፡
ባለፋት አስርት ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው የንግድ አጋርነት በአፍሪካ ትልቁ ትብብር መሆኑን በመግለጽ፤ የቻይና ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አብዮት የጎላ አበርክቶ ነበራቸው ብለዋል፡፡
በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በብረታ ብረት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ በሲሚንቶ እና ኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች በመሳተፍ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና የቻይና ኩባንያዎች መካከል የተፈረመው የትብብር ስምምነት በብሪክስ ማህበረሰብ መካከል ያለውን የአምራች ኢንዱስትሪ እድገት ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራት የሚችሉበት የተሟላ ሥነ ምህዳር መፈጠሩን ገልጸው፤ ለአፍሪካና ለብሪክስ ማህበረሰብ የጋራ ዕድገትና ብልጽግና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የኢትዮጵያና ቻይና ባለሃብቶች ትብብር መሆኑን በማንሳት፤ ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለግል ባለሃብቱ ትኩረት እንደሚሰጥ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ባለፉት ዓመታት መንግስት የግል ባለሃብቶችን ለማሳደግ የህግ ማሻሻያን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በዓለም ላይ ከሰው ሀይል ጥገኝነት የተላቀቀ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የኢንዱስትሪ ልማት እየተስፋፋ መሆኑን በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ወይም ማላመድ እንዳለባት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደ ቻይና ካሉ ያደጉ ሀገራት ጋር በትብብር መስራት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የብሪክስ ፓርትነር ኢኖቬሽን ማዕከል ዋና ዳይሬክተር እና የዣሚን ከተማ ምክትል ከንቲባ ዡዋንግ ሮንግሊንግ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመነት ትስስር በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል አካታችና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር መኖሩን ገልጸው፤ በግል ኩባንያዎች መካከል የተፈረመው ስምምነት ቴክኖሎጂን መሰረተ ያደረገ የኢንዱስትሪ ልማትን ማስፋፋት ያስችላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የግሉ ዘርፍ ትብብር ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል፡፡