ቀጥታ፡

የፕሮጀክት ግንባታ ባለድርሻ አካላት በሰዎች ላይ የሚደርስን ጉዳት በመቀነስ ለግንባታ ደኅንነት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል -ኢንጂነር መስፍን ነገዎ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፦የፕሮጀክት ግንባታ ባለድርሻ አካላት የጥንቃቄ መርህን በመከተል በሰዎች ላይ የሚደርስን ጉዳት በመቀነስ ለግንባታ ደኅንነት ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ( ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር በግንባታ ደህንነትና ጤና ጥንቃቄ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረመዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በፈጣንና እመርታዊ ለውጥ እያለፈ ነው ብለዋል።


 

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በኢኮኖሚ ዕድገትና በስራ ዕድል ፈጠራ አዎንታዊ ሚና ቢኖረውም በፕሮጀክት ግንባታ ሂደት በሚፈጠር የደኅንነት ጥንቃቄ ጉድለት በሰዎች ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ገልጸዋል።

የትብብር ስምምነቱም በፕሮጀክት ግንባታ ሂደት በደኅንነት ጥንቃቄ ጉድለት በሰዎች ላይ የሚከሰትን ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በፕሮጀክት ግንባታ ወቅትም ለሠራተኞች የደኅንነት ግንዛቤ በመስጠት የስራ ላይ እንቅስቃሴ የጥንቃቄ መርሆችን እንዲከተሉ ማስገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ፤ በግንባታ ወቅት በሰዎች ላይ የሚደርስ ሞትና የአካል ጉዳት በህንፃ አዋጆችና ደንቦች አተገባበር ክፍተት የሚመነጭ ነው ብለዋል።


 

በዚህም የሥራ ተቋራጮች ለሠራተኞች የግንባታ ደኅንነትና የጤና ጥንቃቄ ግብዓቶችን በማቅረብ በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ የሚደርስን ጉዳት ማዳን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። 

በቀጣይም ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ተቋራጮች፣ ኮንትራክተሮችና የዘርፉ ተዋናዮች የደኅንነትና ጤና ጥበቃ ሥርዓት ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ህይወት ሳሙኤል፤ በመዲናዋ የግንባታ ፈቃድ የተሰጣቸው በርካታ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በፕሮጀክት የግንባታ ሂደትም ሰዎችን ለሞትና የአካል ጉዳት የሚያጋልጡ የደኅንነት ጥንቃቄ ጉድለቶችን ለማስተካከል ቀጣይነት ያለው ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

የትብብር ስምምነቱም በመዲናዋ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የተሰማሩ አካላት የደኅንነትና የጤና ጥንቃቄ ሥርዓትን እንዲከተሉ ለማስቻል እንደሚያግዝ አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር የሱፍ መሀመድ፤ የትብብር ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ በግንባታ ወቅት የሚፈጠሩ የጥንቃቄ ጉድለቶችን ለማስተካከል እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም