ለአፍሪካ የረጅም ጊዜ የፍትሕ መሻት ጥያቄ ግማሽ መፍትሔ የለም - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ የረጅም ጊዜ የፍትሕ መሻት ጥያቄ ግማሽ መፍትሔ የለም - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2018 (ኢዜአ)፡- ለአፍሪካ የረጅም ጊዜ የፍትሕ መሻት ጥያቄ አቋራጭ ወይም ግማሽ መፍትሔ የለም ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አስገነዘቡ።
ፕሬዚዳንት ታዬ በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያን አቋም በንግግር አቅርበዋል።
በንግግራቸው፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትን ለማሻሻል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
በማሻሻያውም ለአፍሪካ ውክልና በምክር ቤቱ በሁለቱም በኩል ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበው፤ ለአፍሪካ የረጅም ጊዜ የፍትሕ መሻት ጥያቄ አቋራጭ ወይም ግማሽ መፍትሔ እንደሌለ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል በዕዳ ስረዛ ዙሪያ አዲስ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ እና በተለይም አፍሪካን ዒላማ ያደረጉ የኃይል እና የንግድ ዕቀባ እርምጃዎች በአፋጣኝ እንዲነሱ ጠይቀዋል።
አክለውም፤ በቀጣናችን ያለውን ዓለም አቀፍ ጸረ ሽብር ዘመቻ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብም በተለይ በሶማሊያ ለተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ ሰጭና አረጋጊ ኃይል ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
ከታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም፤ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ በፈረንጆቹ ጥቅምት 2024 ወደ ተግባር መግባቱን እና የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን ወደ መቋቋም ደረጃ መቃረቡን አስረድተዋል።
የሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቁ፤ በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ላልሆኑ ኢትዮጵያውያን ንጹህ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ግድቡ በውኃ እጥረት ውስጥ ለሚኖሩ ወገኖቻችን ንጹህ ውኃ ለማቅረብ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና አጠቃላይ ልማትን እውን ለማድረግ አቅማችንን ያሳድጋል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ግድቡ ለሰፋፊ ክልላዊ ትስስር ተስፋን የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘው ከፍተኛ ድጋፍ እና ትብብርም በናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ትብብር ለመፍጠር የሚያነሳሳ መሆኑን ነው ያነሱት።