ወላይታ ድቻ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ወላይታ ድቻ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2018 (ኢዜአ)፦ ወላይታ ድቻ የ2025/26 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከሊቢያው አል-ኢትሃድ ጋር ዛሬ ያከናውናል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በትሪፖሊ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ይካሄዳል።
ቡድኖች ከሳምንት በፊት በአበበ በቂላ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው ይታወቃል።
ወላይታ ድቻ ባለፉት ሶስት ቀናት በትሪፖሊ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ተጋጣሚው አል-ኢትሃድም ከመጀመሪያው ጨዋታ መልስ በትሪፖሊ ዝግጅቱን አድርጓል።
በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ወላይታ ድቻ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በመጨረሻው ዙር ከግብጹ አል ማስሪ ጋር ይገናኛል።
ወላይታ ድቻ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።