ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አገልግሎት መጠቀም የሚያስችሏትን ተጨባጭ እርምጃዎች እየወሰደች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አገልግሎት መጠቀም የሚያስችሏትን ተጨባጭ እርምጃዎች እየወሰደች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሩሲያ እየተካሄደ ባለው የዓለም የአቶሚክ ሳምንት(World Atomic Week) ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች በነቃ ሁኔታ ሀገራቸውን ለመቀየር ተነስተዋል፣ ከተሞቻችን እየዘመኑ ነው፤ ኢንዱስትሪያችንም እያደገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓለም ደረጃ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ኢኮኖሚዎች መካከል አንዱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህልማችን አስተማማኝ፣ ከፍተኛ ንጹህና በየጊዜው የሚያድግ ኢነርጂ ማግኘት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሃይድሮ ፓወር፣ ፀሐይ እና ነፋስ አሁን ያለንበት ደረጃ ቢያደርሱንም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ላለን እቅድ በቂ አይደሉም ነው ያሉት።


 

ኢትዮጵያ ከ10 ዓመት በላይ የአረንጓዴ ኢነርጂን በመጠቀም ተምሳሌታዊ ተግባር ማከናወኗን ገልጸው በአፍሪካ ትልቁ ግድብ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቁርጠኝነታችን ምልክት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለመቀየር ያሉ እድሎችን እየተመለከትን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእነዚህ አማራጮች አንዱ የኒውክለር ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸዋል።

የኒውክለር ቴክኖሎጂ አስተማማኝ እና ዝቅተኛ ብክለት ያለው የኃይል አማራጭ መሆኑን ጠቅሰው የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የህክምና ባለሙያዎች ቴክኖሎጂ እንዲታጠቁ፣ ለውሃ አስተዳደርና ለሳይንቲስቶች የመፍጠር አቅማቸውን የበለጠ እንደሚያሳድግም አብራርተዋል።

ለኢትዮጵያ ኒውክለር ኢነርጂ ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዜጎቻችን በተለያዩ መስኮች ይጠቅማሉ፤ ተማሪዎች አቅማቸውን እንዲጠቀሙና ለታማሚዎች ፈውስን የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የኒውክለር ኃይል አማራጭን ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ የመጠቀም አካሄድን እንደምትከተል ገልጸው በጥንቃቄ በሚመራ እቅድ፣ ከፍተኛ የደህንነት ደረጃን በማረጋገጥና ሀገር በቀል ጠንካራ የአቅም ግንባታ እንደምታከናውን ገልጸዋል።


 

ለኢትዮጵያ የኒውክለር ኃይል በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን የነቃ ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችላት ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ለ80 ዓመታት የኒውክለር ኢንዱስትሪን የተጠቀመችው ሩሲያ ሳይንስ ከራዕይ ጋር ሲጣመር የሚያስገኘውን ውጤት በተግባር አሳይታለች በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ለአፍሪካ ምሳሌ በሆነ መልኩ ያላትን አጋርነት የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች ነው ያሉት።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይዘን ቆመን አንጠብቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኒውክለር ኢነርጂ የረጅም ጊዜ ልማትን ለማረጋገጥ፣ የኃይል ብዝሃነትን ለማስፋትና የኢትዮጵያን አቅሞች ወደ ውጤት ለመቀየር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ግባችን ግልጽ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ መገንባት የምትፈልገው የኒውክለር ፕሮግራም ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ግልጽነት የተሞላበትና ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኢነርጂ (አይኤኢኤ) ለኢትዮጵያ የኒውክለር ፕሮጀክት በአጋርነት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የኒውክለር ኃይል ለመገንባት ተጨባጭ እርምጃዎች እየወሰደች መሆኑንና ከሩሲያ ጋር በመሆን የኒውክለር መሰረተ ልማት ለመገንባት፣ የሰው ኃይል ለማሰልጠንና የቁጥጥር የህግ ማዕቀፎችን ለማጠናከር በእቅድ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኒውክለር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል እንደሚቋቋም ጠቁመውም የኒውክለር ኢነርጂ ሉዓላዊነትን እንዲያጠናክር፣ እድገትን የሚደግፍ እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ ማገልገል የሚያስችሉ ተቋማት እየገነባን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በመከባበርና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትብብር ለመፍጠር ቆርጣ መነሳቷን ገልጸው በኒውክለር ቴክኖሎጂ ሽግግርና ስልጠና ከሌሎች አጋሮች ጋር በትብብር ለመስራት ትሻለች ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም