ቀጥታ፡

የፕላስቲክ አምራቾች ከብክለት የጸዳ የአመራረት ሥርዓት እንዲከተሉ ድጋፍ ይደረጋል - የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦የፕላስቲክ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከብክለት የጸዳ የአመራረት ሥርዓት እንዲከተሉ የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚደረግ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ዙሪያ ከፕላስቲክ ከረጢት አምራች ኢንዱስትሪና ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

በዚሁ ጊዜ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ፤ የሕግ ማሻሻያን ጨምሮ ጽዱ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችሉ አስቻይ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ብለዋል።

በቅርቡም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ የፕላስቲክ ምርቶችን ሙሉ ለሙሉ የሚከለክል እንዳልሆነ አስረድተዋል።

አዋጁም ከአፈር ጋር ሳይዋሃዱ ለበርካታ ዓመታት ቆይተው ብክለትን የሚያስከትሉ የፕላስቲክ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የሚከለክል ድንጋጌ መያዙን ገልጸዋል። 

በዚህም የፕላስቲክ አምራቾች በተሻሻለው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ መሰረት ምርቶቻቸውን ተመልሶ ጥቅም በሚሰጡ ዕቃዎች መቀየር እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ፕላስቲክ አምራቾች በበኩላቸው፤ የተሻሻለው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ የዜጎችን ጤንነት መጠበቅ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በአዋጁ የትግበራ ሂደትም አካባቢን የማይበክል የምርት ሥርዓትን በመከተል ተመልሰው ጥቅም የሚሰጡ ዕቃዎችን ለማምረት የዝግጅት ጊዜ ድጋፍና ክትትል እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ንጉሱ ለማ፤ የፕላስቲክ ምርቶች የአካባቢ ብክለትን በማስከተል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ያስከትላሉ ብለዋል።


 

ለዚህም በቶሎ የማይበሰብሱ ፕላስቲክ ምርቶች ላይ ዕገዳ መጣል ለአካባቢ ደኅንነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው፤ በአዋጁ የትግበራ ሂደት ፕላስቲክ አምራቾች ለሚያጋጥማቸው ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።


 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ በማጠቃለያ ሃሳባቸው፤ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም የሚሰጡ ፕላስቲክ አምራቾችን በገበያ ትስስርና ልምድ ልውውጥ ለማበረታታት ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም