ቀጥታ፡

የመዲናዋን የህዝብ ትራንስፖርት የሚያዘምኑ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚያዘምኑ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን እና ባዝራ ሞተርስ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ማዘመን የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ ወቅት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ያብባል አዲስ፤ በመዲናዋ በኮሪደር ልማት የትራንስፖርት አገልግሎቶችን የሚያሳልጥ ውብ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል ብለዋል።


 

በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የመሰረተ ልማት ተግባራትም መዲናዋን ውብ ገጽታ በማላበስ ለነዋሪዎች ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሻሻልም ከብክለት የጸዱና ምቹ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማቅረብ ነዋሪዎች እንዲገለገሉ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ትብብሩ ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን በአዳዲስ አውቶብሶች በመቀየር የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመን ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ተሽከርካሪዎች የአየር ብክለትን የሚያስከትሉ፤ ለባለንብረቶችም አዋጭ ያልሆኑና ለከተማዋ ገፅታም የማይመጥኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከተቋማቱ ጋር የተደረገው የትብብር ስምምነትም ባለንብረቶች አሮጌ ተሽከርካሪዎቻቸውን በአዲስ መቀየር እንዲችሉ መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የመዲናዋን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በማሻሻል የክፍያ ስርዓቱን የማዘመን ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ብርሃኔ ዘውዴ፤ የትብብር ስምምነቱ የመዲናዋን ውብ ገጽታ የሚመጥኑ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ወደስራ ለማስገባት ጉልህ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።


 

የባዝራ ሞተርስ ዋና ስራ አስኪያጅ ያየህይራድ አስናቀ (ዶ/ር)፤ በተፈጸመው የትብብር ስምምነት መሰረት ከተማዋን የሚመጥኑ ተሽከርካሪ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም