ቀጥታ፡

ወጣቶች በዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ያላቸውን ክህሎት ለማዳበር እየተሰጠ ያለው ስልጠና መጠናከር አለበት- ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ወጣቶች በዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ያላቸውን ክህሎት ለማዳበር እየሰጠ ያለውን ስልጠና አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።

ኢንስቲትዮቱ ለአንድ ወር በዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያ ለወጣት ተማሪዎች በሰመር ካምፕ ሲሰጥ የነበረውን ሥልጠና አጠናቋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ዲፕሎማሲ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ነው።

በዚህ ረገድ በዘርፉ ብቁ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በክረምት መርሃግብር ብቁ የሆኑ ዲፕሎማቶችን ለማፍራት በወጣቶች ላይ የጀመረው ተግባር አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

መርሃግብሩ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ዲፕሎማሲ ሀገራችን የሰነቀችውን የብልፅግና ራዕይ ለማሳካት ቁልፍ ሚና ካላቸው ዘርፎች መካከል ግንባር ቀደም ነው።

በሁለትዮሽና በባለብዙ መድረኮች ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ የተጽእኖ አድማሷ እንዲሰፋ፤ ለዓለም ሰላምና የጋራ በሆኑ የአለም ችግሮች ዙሪያ የሀገራት ትብብር እንዲጠናከር በማድረግ የተረጋጋና ሰላማዊ አለም ለመፍጠር የሚያግዝ እንደሆነም ገልፀዋል።

በዚህ ሂደት ወጣቶች ዲፕሎማሲን መሳሪያ አድርገው የውጭ ግንኙነት ስራን የሚያግዝ ሀይል መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል።


 

የዲፕሎማቲክ ክህሎቶቹን ያዳበረ፣ በዲጂታል ዲፕሎማሲው የሀገሩን ጥቅም የሚያቀነቅንና የሚደግፍ ወጣት መፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ የክረምት የወጣቶች የዲፕሎማሲ ስልጠና ፕሮግራም በመቅረፅ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው በዚህ ስልጠና 50 ተማሪዎች በዝንባሌያቸው ተመርጠውና በጥብቅ ውድድር ተመልምለው ስልጠና በመውሰድ ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

ለአንድ ወር በተሰጠው ስልጠና፣ በሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች፣ በሁለትዮሽና በባለብዙ ዲፕሎማሲና በአፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካ እና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች በዘርፉ ሰፊ እውቀትና ልምድ ባካበቱ አሰልጣኞች እንዲወስዱ ተደርጓል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም