ቀጥታ፡

የቆዳ ጤንነትን እንዴት መጠበቅ ይቻላል?

በራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል የቆዳ እና አባላዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት ዶክተር አደራጀው ብርሃን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የቆዳ ላይ ጤና ችግር ስለሚያስከትሉ ሁኔታዎች እና መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ አብራርተዋል።

👉 የቆዳ አገልግሎት ምንድን ነው?

•  ዶክተር አደራጀው እንደሚሉት፤ ቆዳን ልክ እንደ አጥር ብንወስደው የውስጥ አካልን ከማንኛውም ውጫዊ ጉዳት መጠበቅ እና መንከባከብ ነው።

•  ስሜትን በማዳመጥ የሰውነት ሙቀትን መቆጣጠርም ሌላኛው አገልግሎቱ መሆኑን አስረድተዋል።

•  በሌላ በኩል የቆዳ ተግባር ውበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሌም ሊደረግለት የሚገባ እንክብካቤ እና ጥንቃቄ መኖሩን መገንዘብ እንደሚገባም መክረዋል።

👉 የቆዳ ጤና በምን ምክንያት ሊጎዳ ችላል?

•  ጤናማ እና መደበኛ የቆዳ ተግባራትን የሚያውኩ ነገሮች የቆዳ ህመም እንደሚባሉ ዶክተር አደራጀው አንስተዋል።

•  የቆዳ ጤና በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚጎዳ ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ውስጣዊ፣ ውጫዊ እና ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙ መንስዔዎች ተብለው በሦስት እንደሚከፈሉ አስገንዝበዋል።

👉 ውስጣዊ መንስዔዎች፦ 

•  በቤተሰብ (በዘር ሐረግ) ውስጥ የቆዳ ጤና ችግር ካለ የመወራረስ ሁኔታ መኖር፤

•  ነጭ የደም ኅዋሶች (ሴሎች) ከመጠን በላይ (አላስፈላጊ) ምላሽ መስጠት፤

•  የሆርሞን ለውጥ መኖር (ለምሳሌ፡- ጉርምስና፣ እርግዝና ወዘተ.)፤

•   የውስጥ ደዌ ህመም እንዲሁም ጭንቀት የቆዳ ጤናን የሚያውኩ ውስጣዊ መንስዔዎች መሆናቸውን ነው ዶክተር አደራጀው ያብራሩት።

👉 ውጫዊ መንስዔዎች፡-

•  ኢንፌክሽኖች (ባክቴሪያ፣ ቫይረስ፣ ፈንገስ ወዘተ)፤

•   ለተለያዩ ኬሚካሎች ተጋላጭ መሆን፤

•  ከልክ ላለፈ ፀሐይ፣ ሙቀት እና ወበቅ መጋለጥ ብሎም በሰውነት ላይ የሚደርሱ ተደጋጋሚ ጫናዎች፤

•  ለተለያዩ ህመሞች የሚወሰዱ (የሚቀቡ) መድኃኒቶች ለቆዳ ህመም ከሚያጋልጡ ውጫዊ መንስዔዎች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

👉 ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙ መንስዔዎች፡-

•  ያልተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት፤

•  ማጨስ እንዲሁም ቆዳን ለማስዋብ በሚል የሚደረጉ አንዳንድ ልማዶች በቆዳ ጤና ላይ ችግር እንደሚያስከትሉ ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ከላይ በሦስት ክፍሎች ሥር የተጠቀሱት እና ሌሎችም ያልተጠቀሱ እንደ አደጋ ያሉ ክስተቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የቆዳ ጤናን እንደሚያውክ ባለሙያው አስገንዝበዋል።

👉 የቆዳ ጤናን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይመከራል?

እንደ ሕክምና ባለሙያው ገለጻ፤ የቆዳ ጤንነትን ለመጠበቅ ቀዳሚው ተግባር ተገቢ እንክብካቤ ነው። በአጠቃላይ ከዚህ ጋር በተያያዘ አራት ምሰሦዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እንደሚከተለው አብራርተዋል።

1ኛ. ቆዳን ከጉዳት መከላከል

•  የፀሐይ መከላከያ መጠቀምን ማዘውተር (ከፀሐይ የሚከላከሉ አልባሳት እና ጥላ መጠቀም።)

•  በተለይም ከ4 እስከ 10 ሠዓት ያለው ፀሐይ በቆዳ ላይ ከባድ የጤና ዕክል ሊያስከትል ስለሚችል መጠንቀቅ።

2ኛ. መደበኛ እና በቂ የቆዳ እንክብካቤ

•  ለቆዳ (በተለይም ለፊት) ተስማሚ የሆኑ የንጽህና መጠበቂያዎች (ሳሙና እና ሌሎችም) ጠዋትና ማታ መጠቀም። 

•  ማለስለሻ መጠቀም።

•  ቆዳን የሚያደርቁና የሚያስቆጡ ነገሮችን በተለይም ፊት ላይ ከመጠቀም መቆጠብ።

3ኛ. ቆዳን ከወደ ውስጥ መንከባከብ

•  በቀን ከ2 እስከ 3 ሊትር ውኃ መጠጣት።

•  የተመጣጠነ ምግብ መመገብን ማዘውተር። በዚህም በቪታሚን ኤ፣ ሲ፣ ኢ እና ሌሎችም የበለጸጉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዓይነቶችን መመገብ ቆዳን ከውስጥ በኩል ለመንከባከብ ይረዳል ብለዋል።

4ኛ. የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል

•  ጭንቀትን ማስወገድ፤

•  አለማጨስ፤

•  በቂ እንቅልፍ መተኛት (ከ7 እስከ 9 ሠዓት መተኛት)፤

•  የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር።

  👉 መደረግ የሌለበት … 

•  ያለምንም የፀሐይ መካላከያ ለረጂም ሠዓት ለፀሐይ ተጋልጦ መቀመጥ።

•  ፊትን በተደጋጋሚ መነካካት።

•  ብጉርን መነካካት፣ ማሸት፣ ማፍረጥ።

•  አዲስ የውበት መጠበቂያ ምርትን ጤናማነት ሳያረጋግጡ መጠቀም። (በተለይም በቀጥታ ፊትን ከመቀባት በፊት እጅ ላይ ወይም ጀርባ ላይ በትንሹ ለጥቂት ቀናት በመቀባት ተስማሚነቱን ማየት ይመከራል ብለዋል ዶክተር አደራጀከው።)

•  በቆዳ ላይ የህመም ስሜት ካለ ወይም ከታዬ ጊዜ ሳያባክኑ የቆዳ ሐኪም ማማከር እንደሚመከር አስገንዝበዋል።

በአጠቃላይ ለቆዳ የሚደረግ እንክብካቤ አንድ ሰሞን ብቻ ሳይሆን ሁሌም መቀጠል ያለበት መሆኑን ሕብረተሰቡ ሊገነዘብና ሊተገብረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም