ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ትንሳኤ ማብሰሪያ ነው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ትንሳኤ ማብሰሪያ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራ አንዴሞ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት "ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ’" የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ አስመርቋል።


 

በመርሃ ግብሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራ አንዴሞ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

"ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ" የሚለው መጽሐፍ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጅማሮው እስከ ፍጻሜው በነበረው ሂደት የሀገር ኩራት መሆኑን የሚዳስስ መሆኑ ተገልጿል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራ አንዴሞ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ትንሳኤ ማብሰሪያ ነው።


 

ግድቡ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የእድገት ጉዞ የሚያስቀጥልና የአገሪቱንና የትውልዱን ትክክለኛ እይታ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

"ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ" መጽሐፍ በቀጣይ ለሚጻፉ መጽሐፎች በመነሻነት የሚያገለግል መሆኑን ጠቁመዋል።

አገሪቱ የተያያዘችው ጉዞ  እውን እንዲሆን ትውልድ ላይ መስራት አለብን ያሉት ምክትል ሰብሳቢው የፕሬስ ድርጅት በዚህ ረገድ ያከናወነው ስራ የሚመሰገን መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን የመልማት ቁጭታቸውን የተወጡበት ትልቅ የታሪክ አሻራ ነው ብለዋል።


 

ግድቡ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ በዚህ ዘመን ትውልድ ለፍፃሜ መብቃቱን በማንሳት፤ የተከፈለውን ዋጋ ለታሪክ መሰነድና መረጃዎችን አደራጅቶ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተሰነደው "ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ" መጽሐፍ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን እውነቷን፣ መሻቷን እና ፖሊሲዋን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ተግዳሮቶችን በማለፍ ለስኬት መብቃቱን ተናግረዋል።


 

የግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸው ለሌሎች ድሎች የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክት የተመረቀበት ቀን ብቻ ሳይሆን የትርክት ለውጥ የተደረገበት ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከጅማሬ እሰከ ፍፃሜው በተለያዩ ቋንቋዎች ዘገባዎችን ተደራሽ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፤ ግድቡን በተመለከተ የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተያየቶችን ስንመክት ቆይተናል ብለዋል።

"ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ"’ መጽሐፍ የህዝቡን የዘመናት ቁጭት የሚዘክር፣ ተጋድሎውን የሚያስታውስ እና የዘመኑ ትውልድ ለድል የበቃበትን መንገድ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ከዓባይ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ማወቅ ለሚፈልግ ምላሽ የሚሰጥ እና ለጥናትና ምርምር ስራዎችም በግብዓትነት የሚያገለግል መሆኑን አንስተዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መጽሐፉ በግድቡ ዙሪያ በርካታ ሀሳቦችን የያዘ መሆኑን ጠቁመው ለምርምርና ለሌሎች ስራዎች በመነሻነት ያገለግላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም