ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሥነ ምህዳር በመፍጠር ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች-ሚኒስትር መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሥነ ምህዳር በመፍጠር ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች-ሚኒስትር መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሥነ ምህዳር በመፍጠር ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በቻይና ኢንዱስትሪና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ሊ ሊቸንግ የተመራ የቢዝነስ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያጠናክሩበት ዕድል ተፈጥሯል።
ቻይና የኢትዮጵያ አጋር በመሆን ለዓመታት መቆየቷን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንቨስትመንት የተመቸ ሥነ ምህዳር ፈጥራለች ብለዋል።
ቻይና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በታዳሽ ሀይል ልማት፣ በመንገድና ባቡር መሰረተ ልማት በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ገንቢ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።
ቻይና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ እድገት የምታበረክተው አስተዋፅኦ ኢትዮጵያን የቀጣናው የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ለጀመርነው ስራ አጋዥ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የኢንዱስትሪ ልማትን ቅድሚያ ሰጥታ እንደምትሰራ ገልጸዋል።
በዚህም ተኪ ምርትን ማሳደግ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ምርት በመጠን፣ በአይነትና ጥራት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን ማሻሻልና የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ መቻሏን ገልጸው፤ ኢትዮጵያን ተገማችና ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
የቻይና ባለሀብቶች ተሳትፎ በየጊዜው እያደገ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የክህሎት ልማት፣ ኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ኢንዱስትሪን ዕውን ለማድረግ በምታደርገው ጥረት የቻይና ባለሀብቶች ሚና የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን መደገፍ የሚያስችል የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ መዘርጋቷን ጠቅሰው፤ ቻይና ብቁ የኢንዱስትሪ አስተዳደር አቅም እንድንገነባ እገዛ አድርጋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ልማት ሰፊ ገበያ፣ የተሟላ መሰረተ ልማት፣ ቴክኖሎጂና ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዳላት ጠቅሰው፣ ቻይናን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የቻይና የኢንዱስትሪና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሊ ሊቸንግ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የቻይና ወሳኝ አጋር መሆኗን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
ቻይና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰው፣ ለኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ቅድሚያ ትሰጣለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ እና ቻይና ትብብር እያደገ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እሴት በሚጨምሩ የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች ላይ በስፋት እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለማነቃቃት ወሳኝ እርምጃ በመውሰዷ ለውጭ ኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆኗን ተናግረዋል።
የዛሬው ውይይትም በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በመፍጠር በዘርፉ ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ትብብር መፍጠር ያስችላል ብለዋል።