ቀጥታ፡

የ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018 (ኢዜአ)፦ የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

በ20 ክለቦች መካከል የሚደረገው ውድድር ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም ይጀመራል።

ሊጉ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን በእያንዳንዱ ምድብ 10 ክለቦች ይገኛሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ፋሲል ከነማ ስሑል ሽሬ፣ መቻል፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ ፣ሃዋሳ ከተማ፣ መቀሌ 70 እንድርታ፣ ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ አንድ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው።

በምድብ ሁለት ነገሌ አርሲ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ሸገር ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ አርባምንጭ ከተማ እና  ቅዱስ ጊዮርጊስ ተደልድለዋል።

የምድብ አንድ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች በአዳማ እና የምድብ ሁለት መርሃ ግብሮች በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ።


 

በምድብ አንድ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ከ ሲዳማ ቡና፣ ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ስሑል ሽሬ ከመቀሌ 70 እንደርታ ፣መቻል ከወላይታ ድቻ  እና ድሬዳዋ ከተማ ከ ሃዋሳ ከተማ ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣  ነገሌ አርሲ ከአርባምንጭ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ ከ ሀድያ ሆሳዕና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሸገር ከተማ እና አዳማ ከተማ ከወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በምድብ ሁለት የሚደረጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ናቸው።

አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ እና ሃዋሳ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች የሚደረጉባቸው ከተሞች ናቸው።

20ዎቹ ክለቦች በ38 የውድድር ሳምንታት 380 ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።

እንደ አስፈላጊነቱ የጨዋታ ቀናት እና ጨዋታ የሚደረግባቸው ቦታዎች ላይ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም