የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የመረጃ ተደራሽነትን በማስፋት የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የመረጃ ተደራሽነትን በማስፋት የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል
ድሬደዋ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦ በሽታን ለመከላከል እና የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የመረጃ ተደራሽነትን በማስፋት የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ጋር በመሆን በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና ሰጥቷል ።
በኢንስቲትዩቱ የማሕበረሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ባለሙያ አቶ አእምሮ ይበልጣል በወቅቱ እንዳሉት፤ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በሙያቸው በመደገፍ ሚናቸውን ይበልጥ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
በድሬዳዋ የተሰጠው ስልጠናም የበሽታ መከላከል መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተገቢውን ዕውቀት ያስጨበጠና ለቀጣይ ተልዕኳቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢንስቲትዩቱ በቀጣይም መሰል የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በድሬዳዋ ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ኢብራሂም አብዱልሐሚድ በበኩላቸው ክረምቱን ተከትሎ የሚከሰቱ የወባ እና መሰል ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የተቀናጀ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
እነዚሕ ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተገነባና የመከላከሉን ስራ በባለቤትነት የሚያግዝ ማሕበረሰብ መፍጠር መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚሕ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በዚሕ ረገድ የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በስልጠናው ላይ በድሬዳዋ እና በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እና አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በቀሰሙት ዕውቀት ታግዘው ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።