ቀጥታ፡

የሰላማዊ ኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለመደገፍ የማይተካ ሚና ይኖረዋል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦ የሰላማዊ ኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ ለመደገፍ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የዘርፉ ተመራማሪ ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ወቅት 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማብሰራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ቀጣይ ብሔራዊ ፕሮጀክቶቹም ሰላማዊ የኒውክሌር ማብላያ፣ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፋብሪካ፣ ግዙፍ የአየር ማረፊያ፣ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ናቸው።

ይፋ ከተደረጉ ፕሮጀክቶች ማካከል ሰላማዊ የኒውክሌር ማብላያ አንዱ ሲሆን ፕሮጀክቱ የሚኖረውን ሀገራዊ ፋይዳ በተመለከተ ኢዜአ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን  እና የዘርፉን ተመራማሪዎች አነጋግሯል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያበሰሯቸው ፕሮጀክቶች ለሀገር ዕድገት ትልቅ ዜና ነው።


 

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ ለሀገር ዘላቂ ልማትና ብልጽግና ወሳኝ ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን አብስራለች ብለዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት 96 ከመቶ በላይ ከውሃ ኃይል የሚመነጭ ነው ብለዋል።

የኒውክሌር፣ የፀሐይ፣ የነፋስና ተጨማሪ የኃይል አማራጮች ልማትም የሀገር ውስጥና የጎረቤት ሀገራትን የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በተለይም ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት ከኃይል አቅርቦት በዘለለ የሀገርን የጤና፣ የግብርና እና ሌሎች የልማት መስኮችን ለማዘመን አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።  

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዎስ፤ የዩራኒየም ማዕድን የኒውክሌር የኃይል አማራጭን ለማልማት ወሳኝ ከሆኑ ማዕድናት ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ የምትገነባው ሰላማዊ የኒውክሌር ማብላያ ፕሮጀክትም የኃይል አቅርቦት አቅምን በማሳደግ ሌላኛው የህዳሴ ግድብ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በዩራኒየም ማዕድን ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ማብላያ ፕሮጀክት ግንባታም የግብርና፣ ህክምና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ተግባራትን ለማዘመን ወሳኝ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።  

በዚህም የኒውክሌር ፕሮጀክት ግንባታን ለማስጀመር አቅም መለየት የሚያስችልና የዩራኒየም ማዕድን የሚገኝባቸውን አካባቢዎች  ልየታ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፤ በታለቁ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ወቅት የተበሰረው ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ብዝኃ የኃይል አማራጭን ለማስፋት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ የውሃ፣ የፀሐይ፣ የነፋስ ኃይል አማራጭን በስፋት በማልማት ጥቅም ላይ እያዋለች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የኃይል አቅርቦት ብዝሃነትን ለማስፋትም የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማትን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የሰው ሃይልና ተያያዥ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። 

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኒውክሌር ማብለያ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ኃላፊ ደረጃው አየለ (ዶ/ር)፤ የበለጸጉ ሀገራት የኃይል ደህንነታቸውን በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት በሁሉም መስክ ዕድገታቸውን እያስቀጠሉ ነው ብለዋል።


 

ሰላማዊ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት ዕቅድ መበሰሩም ለኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ስኬታማ የጥናትና ምርምር ለማከናወን ወርቃማ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማትም የግብርና፣ የህክምና፣ የፈጠራና ምርምር ተግባራትን በማከናወን ዕድገትን ለማሳለጥ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም