ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የንጹህ መጠጥ ውኃን ተደራሽ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው   

ሮቤ ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ። 

በባሌ ዞን ጎሮ ወረዳ መልካ ቡታ ከተማ ከ86 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። 


 

የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ እንዳሉት በክልሉ የማህበረሰቡን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው። 

በክልሉ በተለይም ባለፉት ዓመታት የንጹህ የመጠጥ ውሃ መሰረተ ልማትን በመገንባት ተደራሽነቱን ማሳደግ መቻሉን አስታውሰዋል። 


 

በክልሉ የክላስተር አደረጃጀትን በማጠናከር በገጠርና በከተሞች የህዝብን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚነት እውን የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። 

ዛሬ ለአገልግሎት የበቃው የውሀ ፕሮጀክት በባሌ ዞን ውሀ ጽህፈት ቤት፣ በአጋር አካላትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን አክለዋል።

በዞኑ ከለውጡ ማግስት ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተሰርተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ያስታወሱት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ ናቸው። 


 

በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክትም የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ ሰባት የውኃ ቦኖዎችን ጨምሮ ለሰውና ለእንስሳት የመጠጥ ውኃ የሚውል ባለ 200 ሺህ ሊትር ውኃ ጋን እንደሚገኝበት የገለጹት ደግሞ የዞኑ ውኃና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ ወርቁ ናቸው። 

ፕሮጀክቱ በፀሃይ ኃይል የሚሰራ በመሆኑ በዘላቂነት ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው ማህበረሰቡም አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። 

የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በአካባቢያቸው ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ከዚህ በፊት የነበረባቸውን ችግር  እንደሚያቃልላቸው ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም