ቀጥታ፡

የአደባባይ በዓላት ኢትዮጵያዊ መልኮቻችንና አብሮነታችንን ለዓለም የምናሳይባቸው መድረኮች ናቸው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦የአደባባይ በዓላት ኢትዮጵያዊ መልኮቻችንና አብሮነታችንን ለዓለም የምናሳይባቸው መድረኮች ናቸው ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል የሚከበርበት የመስቀል አደባባይን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ዛሬ ጠዋት የማጽዳት መርሃ ግብር ተከናውኗል። 


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ወቅት፤ የመሰቀል ደመራ በአደባባይ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡

የአደባባይ በዓላት ኢትዮጵያዊ መልኮቻችንና አንድነታችንን ለዓለም የምናሳይባቸው መድረኮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የመስቀል ደመራ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ በመሆን የአብሮነት በዓል መሆኑን ገልጸው፤ ሀብትነቱ ከእምነቱ ተከታዮች ባሻገር የመላው ኢትዮጵያውያን ነው ብለዋል።

በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ በዓሉን በድምቀት ለማክበር እቅዶችን አዘጋጅቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

የዛሬው የጽዳት መርሃ ግብርም የዚሁ እቅድ አካል መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ላይም በዓሉ በድምቀት እንዲከበር የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በዓሉ የሚከበርባቸው ስፍራዎች ከአደጋ ስጋት ነጻ ሆነዋል፤ ገጽታቸውም ተቀይሯል ነው ያሉት፡፡


 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእቅድና ልማት መምሪያ ሃላፊ መልዓከ ህይዎት ቆመስ አባ ወልደየሱስ ሰይፉ በበኩላቸው፤ መስቀል የአብሮነት አሴቶቻችንን ከፍ የሚያደርግ የፍቅር በዓል ነው ብለዋል፡፡

በዓሉ ከኃይማኖታዊ አስተምህሮው ባሻገር የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ መተባበርና አብሮነት የሚገለጽበት ነው ብለዋል።

በዛሬው የጽዳት መርሃ ግብር ለተሳተፉ ሁሉ እንዲሁም ከተማ አስተዳደሩ በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ወክለው ንግግር ያደረጉት ሃጂ አወል ሃምዛ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በህብረት ህዳሴ ግድብን በስኬት አጠናቀናል ብለዋል፡፡  


 

እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን አብሮነት ነው፤ አብሮነት ያደምቃል ወደ የጋራ ስኬትም ያድርሳል ነው ያሉት፡፡

በጽዳት መርሃ ግብሩ ከተሳተፉ የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል አቶ ሀብቴ ቶፊቅ በመርሃ-ግብሩ የተገኘሁት ለክርስቲያን ወገኖቼ አብሮነቴን ለማሳየት ነው ብለዋል፡፡  


 

ሌላዋ የመርሃግብሩ ተሳታፊ ገነት ወጊ በበኩላቸው፤ በጽዳት መርሃ ግብሩ ባዩት መተባበር መደሰታቸውን ገልጸው፤ በዓሉን ያለምንም የሐይማኖት ልዮነት ከጎረቤቶቻችን ጋር በመሆን የምናሳልፍ ይሆናል ብለዋል፡፡


 

የደመራ ማክበሪያ ስፍራ ጽዳት ላይ ተሳታፊ በመሆኔ እጅግ ተደስቻለሁ ያለው ደግሞ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ወጣት አበበ ጡዴላ ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም