የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የትኛውንም ግዳጅ በአስተማማኝ ብቃት መወጣት የሚችል ጠንካራ ሠራዊት ተገንብቷል - የመከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የትኛውንም ግዳጅ በአስተማማኝ ብቃት መወጣት የሚችል ጠንካራ ሠራዊት ተገንብቷል - የመከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት በማስጠበቅ የትኛውንም ግዳጅ በአስተማማኝ ብቃት መወጣት የሚችል ጠንካራ ሠራዊት መገንባቱን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች አስታወቁ።
የመከላከያ ሠራዊት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ እና የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጌትነት አዳነ በመከላከያ ሠራዊት ቁመና እና የጦር መኮንኖች ሹመትን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብር፣ አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም በአመራር ልህቀት በአስተማማኝ ደረጃ ጠንካራ ሠራዊት እየተገነባ ነው።
በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሠራዊት በትጥቅ የተሟላ፣ አስተማማኝ ቁመና ያለው ጠንካራ የሀገር ዘብ መገንባቱን አመልክተው፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ግን የሚያስቡት የተዳከመች ሀገር ማየት እንደነበር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች የመከላከያ ሠራዊት ግዳጁን በአግባቡ መፈጸም የማይችል እንዲሆን በማለም የጥፋት ግባቸውን ለማሳካት ቅዠት ውስጥ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም በአስተማማኝ መልኩ የሚጠብቅ ጠንካራ ቁመና ላይ የሚገኝ የሀገር ዘብ መገንባቱንም ነው የገለጹት።
ለአብነትም በየጊዜው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል የሀገራቸውን ሉዓላዊ አንድነት እያስጠበቁ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ተቋም ማንኛውንም የኢትዮጵያን ጠላት ሀሳብ ማክሸፍ የሚችል ጠንካራ አደረጃጀት ተላብሶ ስኬታማ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው፤ መንግስት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቅ የሚያስችሉ ግዙፍ የልማት ዕቅዶች መያዙን ገልጸዋል።
በዚህም የመከላከያ ሠራዊት በህዝብ የተመረጠን መንግስት እንደሚያገለግል ተቋም በሁሉም መስክ በአስተማማኝ ዝግጅትና የማድረግ አቅም ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት በመፃረር በተቃርኖ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችንም አደብ በማስገዛት የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ የሚገኝ ሠራዊት መሆኑን አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ ለጦር መኮንኖች መስከረም 10 ቀን 2018 ዓ.ም የተሰጠውን ሹመት አስመልክቶ እንደገለጹት፤ ሹመቱ ከዚህ ቀደም ለተመዘገበው ስኬት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ግዳጅና ተልዕኮ መኖሩን ታሳቢ ያደረገ ነው።
ለሠራዊቱ ወታደራዊ የጦር መኮንኖች የተሰጠው ሹመት የሠራዊቱን የማድረግ አቅም በማሳደግ ከብረት የጠነከረ ኃይል የመገንባት አካል ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጌትነት አዳነ፤ ለሠራዊቱ የጦር መኮንኖች የተሰጠው ሹመት በሥነ-ልቦና የበለጠ በመገንባት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማጽናት ቀላል ትርጉም የሚሰጠው አይደለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት በርካታ የበሬ ወለድ ውዥንብር መረጃዎችን በጽናት በመወጣት በተግባር ተፈትኖ ያለፈ መሆኑንም አስግንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅትም ፀረ-ሰላም ኃይሎችን አደብ በማስገዛት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊ አንድነት በማስጠበቅ ለገባለት ቃል ኪዳን ታምኖ እያገለገለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አቅራቢነት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 10 ቀን 2018 ዓ.ም ለመከላከያ ሠራዊት የጦር መኮንኖች ሹመት መስጠታቸው ይታወሳል።