የሐረማያ ሐይቅ የጎብኝዎች መዳረሻ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
የሐረማያ ሐይቅ የጎብኝዎች መዳረሻ ሆኗል

ሐረማያ መስከረም 15/2018 (ኢዜአ)፡- የሐረማያ ሐይቅ የጎብኝዎች መዳረሻ በመሆን በዘርፉ ለተሰማሩ አካላትም የገቢ ምንጭ ሆኗል።
"ወየው ሐረማያ የሐረር ሲሳይ
ባህርም እንደሰው ሞት ይሞታል ወይ?
ተብሎ የተገጠመለት እና ወደ ታሪክነት ተቀይሮ የነበረው የሐረማያ ሃይቅ መልሶ ነፍስ ዘርቶ በማንሰራራት አይነተኛ የቱሪስት መስህብ ሆኗል።
የሐረማያ ሐይቅ ለ17 ዓመታት ደርቆና ነጥፎ የነበረ ቢሆንም በዙሪያው በሚገኙ ተፋሰሶች ላይ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ሃይቁ ወደ ነበረበት የተመለሰ ሲሆን የውሃው መጠንም ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል።
በዚህም ሃይቁ የጎብኝዎች መዳረሻ እየሆነ በመምጣቱ ደግሞ በዘርፉ ተደራጅተው የተሰማሩት ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ ካነጋገራቸው መካከል ወጣት እስክንድር ዩስፍ፤ የሐይቁ መመለስ ከውጪ ሀገርና ከሀገር ውስጥ ለጉብኝት የሚመጡ ሰዎች የሚጎበኝ የዓይን ማረፊያ ሆኗል።
በማህበር ከተደራጁ ጓደኞቹ ጋር ቱሪስቶችን በማስጎብኘትና በአካባቢው በማዝናናት ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስቶ ሐይቁን የመንከባከብ ስራም እያከናወንን እንገኛለን ብሏል።
የሐረማያ ሐይቅ ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለሱ እኔና ቤተሰቦቼን ጨምሮ ሌሎች ወጣቶች በተለያየ ዘርፍ የስራ እድል እንድናገኝ እድል ፈጥሯል ያሉት ደግሞ በሐይቁ በአስጎብኚነትና የአሳ ምግብ ቤት ከፍተው የሚሰሩት አቶ ረመዳን አሊ ናቸው።
ሐይቁ የጎብኚዎችን ቀልብ እየሳበና በበርካቶች እየተጎበኘ መሆኑን አንስተው፤ እንደ በፊቱ ሐይቁ ጉዳት እንዳይገጥመው የእንክብካቤ ስራን እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
በኦሮሚያ ክልል የማያ ከተማ አስተዳደር የቱሪዝም ጽህፈት ቤት ተወካይ ወይዘሮ ፎዚያ መሐመድ፤ ሐይቁ ከተመለሰ ጀምሮ ወደ ስፍራው የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ለማኅብረሰቡ እና በዘርፉ የተሰማሩ ባለ ድርሻ አካላትን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመው በተለይ ሐይቁ ተመልሶ ጉዳት እንዳይጋረጥበት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የእንክብካቤ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በከተማው የቱሪስቱን ቆይታ ለማራዘምም ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲሰማሩ የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሐረማያ ሃይቅ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም መምህር ዲኔ ረሺድ ለ17 ዓመታት ደርቆ የነበረው የሐረማያ ሃይቅ ዩኒቨርሲቲው በጥናት ላይ በመመስረትና ከህብረተሰቡ ጋር ባከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃና አረንጓዴ አሻራ ስራዎች ሐይቁ እንዲመለስ አስችሏል።
በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የተመለሰው የሐረማያ ሐይቅ በውሃ ላይ የተመሰረተ የቱሪዝም ዕድል እየፈጠረ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሃይቁ በደለልና ቆሻሻ እንዳይሞላ በሃይቁ ዳርቻ የተለያዩ ስትራክቸሮችን የመስራትና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመስጠት እንዲሁም ውሃ ቆጣቢ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ የማድረግና የቁሳቁስ ድጋፍ ስራዎች መከናወኑን ተናግረዋል።