ኢትዮጵያ የአየር ጥራትን ለማሻሻል እየወሰደች ያለው እርምጃ እና ቁርጠኝነቷ የሚደነቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ጥራትን ለማሻሻል እየወሰደች ያለው እርምጃ እና ቁርጠኝነቷ የሚደነቅ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ጥራትን ለማሻሻል እየወሰደች ያለው እርምጃ እና ያላት ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ሲል ዓለም አቀፉ የምርምር ተቋም የስቶክሆልም ኢንቫይሮመንት ኢኒስቲትዩት ገለጸ።
የአየር ጥራት አየር ምን ያህል ከብክለት ነጻ ነው? የሚለው የሚለካበት መንገድ ነው።
ሀገራት እና ተቋማት የአየር ጥራት መለኪያዎችን በማዘጋጀት አየሩ ንጹህ ነው ወይስ ተበክሏል የሚለውን በመመዘን ጥራቱን ለማሻሻል ይሰራሉ።
የአየር ጥራት መሻሻል የበሽታ ተጋላጭነት ለመቀነስ፣ ለከባቢ አየር ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ወሳኝ ሚና አለው።
እ.አ.አ በ1989 የተመሰረተው የስቶክሆልም ኢንቫይሮመንት ኢኒስቲትዩት የአየር ንብረት፣ ከባቢ አየር እና የዘላቂ ልማት ፈተናዎች እንዲፈቱ በጥናት እና ምርምር ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ የመፍትሄ ሀሳቦችን ያቀርባል፤ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ያደርጋል።
ዓለም አቀፍ የሳይንስ ፖሊሲ ተቋሙ ከሚያደርጋቸው ድጋፎች መካከል ሀገራት የአየር ጥራት እንዲያሻሻሉ ማገዝ ነው።
የስቶክሆልም ኢንቫይሮመንታል ኢኒስቲትዩት የአየር ጥራት ባለሙያ እና ተመራማሪ ንጎንጋንግ ዋንጂ ዳኑብ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ የአየር ጥራትን ለማሻሻል ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ጥራትን አስመልክቶ በየጊዜው መረጃን በማሰባሰብ ብክለትን አስቀድሞ ለመከላከል እያከናወነች ያለው ስራ አበረታች ነው ብለዋል።
በተቋም ደረጃ መረጃዎችን ለፖሊሲ ግብአትነት ለማዋል ያለውን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል።
የአየር ጥራት አስተዳደር እና የጥራት መቆጣጠሪያ እቅድ ማዘጋጀት የአየር ብክለትን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ኢኒስቲትዩቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በመዲናዋ የአየር ጥራት መረጃን በማሳባሰብና የአየር ጥራት ቁጥጥር እያከናወነ ያለው ስራ እየደገፈ እንደሚገኝ ነው ባለሙያው የገለጹት።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሚያበለጽጋቸውን ቴክኖሎጂዎች ጨምሮ ኢትዮጵያ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ያሏትን አቅሞች የአየር ጥራት መረጃዎችን በየጊዜው በመሰብሰብ ብክለትን ለመቀነስ አበክራ መስራት እንዳለባት መክረዋል።
የአየር ጥራትና የአየር ንብረት መረጃዎች በተቀናጀ መልኩ በመጠቀም ብክለትን መከላከል ላይ ሁሉን አቀፍ ውጤት ለማምጣት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የስቶክሆልም ኢንቫይሮመንታል ኢኒስቲትዩት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ ሀገራት የአየር ጥራት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
በብሄራዊ የአየር ጥራት መለኪያዎች ቀረጻ እና ትግበራ የፖሊሲና አቅም ግንባታ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ሀገራት የአየር ጥራት መረጃዎቻቸውን ከብሄራዊ የአየር ንብረት አገልግሎቶች ማዕቀፍ ጋር በማስተሳሰር ላይ እንደሚገኙም ነው ባለሙያው ያብራሩት።
ሀገራት በአየር ትንበያ ጣቢያዎቻቸው ከአየር ንብረት መረጃዎቻቸው ጋር የአየር ጥራት መረጃዎችን አጣምሮ በመጠቀም የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንዲሰሩና ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚያደርጉትን ሽግግር እንዲያፋጥኑ አሳስበዋል።
አፍሪካውያን የአየር ጥራት ጉዳይን በተቋማማዊ መዋቅር እና ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ለማካተት የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።