የስልክ፣ የታብሌት፣ የኮምፒውተር እና ስክሪን ጨረር እና የዐይን ጤና - ኢዜአ አማርኛ
የስልክ፣ የታብሌት፣ የኮምፒውተር እና ስክሪን ጨረር እና የዐይን ጤና
የስልክ፣ ታብሌት፣ ኮምፒውተር እንዲሁም ስክሪን አጠቃቀምን በደቂቃዎች መገደብ ካልተቻለ የዐይን ጤና እንደሚታወክ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ኦፕቶሜትሪ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት እና ኦፕቶሜትሪስት በቃሉ ጌታሁን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የዐይን ጤና በምን ምክንያት ሊጎዳ ይችላል? የዐይን ጤና እንዳይጎዳ ምን መደረግ አለበት? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በተጨማሪም ሰዎች ብዙ ጊዜ ከስልክ፣ ታብሌት እና ኮምፒውተር ጋር ሲያሳልፉ በዐይናቸው ላይ የሚደርሰው ጉዳት ምንድን ነው? አጠቃቀማቸው እንዴት ቢሆን ይመከራል? በዓለም ብሎም በኢትዮጵያ ምን ያህል ሰዎች ከስክሪን ጋር በተያያዘ ለዐይን ጤና ችግር ይጋለጣሉ? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
👉 የዐይን ጤና በምን በምን ምክንያት ሊጎዳ ይችላል?
ኦፕቶሜትሪስት በቃሉ እንደሚሉት የዐይን ጤና ችግር ተፈጥሯዊ በሆኑ እና ባልሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል።
• ለአብነትም፡- በዕድሜ መጨመር፣ ከቅርብ ቤተሰብ በውርስ፣ በአደጋ፣ በጎጂ የፀሐይ ጨረር (አልትራቫዮሌት)፣ የተመጣጠነ ምግብ ባለመመገብ እንዲሁም በንፅህና ጉድለት የዐይን ጤና ሊታወክ እንደሚችል ጠቅሰዋል።
• በተጨማሪም በሌሎች የጤና ችግሮች የጎንዮሽ ጉዳት (ለምሳሌ በስኳር ህመም፣ በደም ግፊት ወዘተ) በመድኃኒት አወሳሰድ ወቅት የዐይን ጤና ችግር ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል።
👉 የዐይን ጤና እንዳይጎዳ ምን መደረግ አለበት?
የዐይንን ጤንነት ለመጠበቅ በተለይም ከተፈጥሯዊ መንስዔዎች ውጭ ያለውን ተጋላጭነት መቀነስ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን ኦፕቶሜትሪስት በቃሉ አስረድተዋል። ለአብነትም፡-
• የተመጣጠነ ምግብ (በቫይታሚን የበለፀጉ ምግቦችን) አዘውትሮ መመገብ፤
• በሐኪም የተፈቀዱ የጨረር መከላከለያ መነጽሮችን መጠቀም፤
• የግል እና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ፤
• የዐይን ምርመራ ማድረግ፤
• የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሠዓትን መገደብ፤
• አካላዊ እንቅስቃሴ ማዘውተር የዐይንን ጤንነት ለመጠበቅ እንደሚያግዙ አብራርተዋል።
👉 ሰዎች ብዙ ጊዜ ከስልክ፣ ታብሌት እና ኮምፒውተር ጋር ሲያሳልፉ በዐይናቸው ላይ የሚደርሰው ጉዳት ምንድን ነው?
የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንደ ልብ ስለተገኙ ብቻ ለረጂም ሠዓታት መጠቀም በሂደት በዐይን ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል በመገንዘብ፤ አጠቃቀምን መገደብ (በሚጠቀሙበት ጊዜ በመሐል ዕረፍት ማድረግ) እንደሚገባ መክረዋል።
ያለ እረፍት አዘውትሮ ለረጂም ሠዓታት መጠቀም ግን ጉዳት እንደሚያደርስ አስገንዝበዋል። ለምሳሌ ከጉዳቶቹ መካከልም፡-
• ምቾት ማጣት (ዐይንን የመቆርቆር ስሜት መሰማት፣ የዐይን መቅላት፣ ማቃጠል፣ ራስ ምታት)፤
• አጣርቶ ማየት አለመቻል፤
• የዐይን ድርቀት፤
• የዐይን ድካም የሚሉትን አብራርተዋል።
👉 የስልክ፣ ታብሌት እና ኮምፒውተር አጠቃቀም በዐይን ላይ ጉዳት እንዳያመጣ እንዴት መሆን አለበት?
• በየ20 ደቂቃው ዐይንን ማሳረፍ፤ ዐይንን ማርገብገብ፤
• ዐይንን ከኮምፒውተር እስክሪን ሁኔታ ጋር ማጣጣም፤
• በሐኪም ፈቃድ የኮምፒውተር ጨረር መከላከያ መነጽሮችን መጠቀም፤
• ማለስለሻ ጠብታዎችን (ቅባቶችን) መጠቀም፤
• ከዐይን ራቅ አድርጎ መጠቀም (ከ50 እስከ 70 ሳንቲ ሜትር)፤
• የዐይን ምርመራ ማድረግ ከስልክ፣ ታብሌት እና ኮምፒውተር አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በዐይን ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት እንደሚቀንስ ኦፕቶሜትሪስት በቃሉ አስገንዝበዋል።
👉 በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ60 እስከ 70 ሚሊየን ሕዝብ (በየዓመቱ 1 ሚሊየን ተጨማሪ ሕዝብ) ከስክሪን ጋር በተያያዘ ለዐይን ጤና ችግር እንደሚጋለጥ ጥናቶች ያመላክታሉ ብለዋል።
👉 በኢትዮጵያም ከኮምፒውተር ተጠቃሚዎች ውስጥ 73 በመቶው የዐይን ጤና ችግር እንደሚያጋጥማቸው ነው ያመላከቱት።