አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ አጠቃላይ የፀጥታ ማስከበር ሥራ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ አጠቃላይ የፀጥታ ማስከበር ሥራ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ አጠቃላይ የፀጥታ ማስከበር ሥራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አስታወቁ፡፡
የጸጥታ ማስከበር ስራው በርካታ የፖሊስ ሠራዊት በማሰማራት ከክልልና ከፌደራል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የመስቀል ደመራ በዓል በስኬት እንዲከናወን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት መሪዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በውይይቱ እንደገለጹት ከሃይማኖት መሪዎች ጋር መወያየቱ በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ያስችላል።
ኮሚሽነር ጀነራል የጸጥታ ማስከበር ስራው አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘና በርካታ የፖሊስ ሠራዊት በማሰማራት ከክልልና ከፌደራል የፀጥታና አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት መሪዎች የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርን በተመለከተ ከፀጥታና ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄዷቸው በርካታ የሕዝብ ንቅናቄ መድረኮች መላው ሕብረተሰብ የበዓሉ ባለቤት በመሆን በስኬት እንዲከበር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዋል።
በዚህ ዓመት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ ባር ኮድ ያላቸው የመኪና ማለፊያ(car pass) እና የክብር እንግዶች የመግቢያ ባጆች መዘጋጀታቸውንም የሃይማኖት መሪዎች አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በመላ ሀገሪቱ ስምሪት ወስዶ ውድ ሕይወቱን እየከፈለ የተካሄዱ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ደህንነታቸው ተጠብቆ በስኬት እንዲጠናቀቁ በማድረጉ ቤተ ክርስቲያኗ ትልቅ ክብር እንደምትሰጥ የሃይማኖት መሪዎቹ ተናግረዋል።