ቀጥታ፡

በክልሎቹና በድሬዳዋ አስተዳደር የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ነገ ይመረቃሉ

መስከረም 14/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት ነገ ይመረቃሉ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሐልጌዮ ጂሎ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ መጀመር የአገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍ የዜጎችን እንግልት እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረ ያልተቀላጠፈ የአገልግሎት አሰጣጥን በሚቀይር መልኩ በቴክኖሎጂ የተደራጀው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ስራ መግባት ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን ባለፈ የተገልጋዮችን ጊዜና ገንዘብ እንደሚቆጥብ ጠቁመዋል።

በማዕከሉ ውስጥ የተለያዩ አገልግሎቶችን በተቀናጀ መንገድ የሚሰጡ የፌዴራልና የክልል ተቋማት መኖራቸውን አመልክተዋል።

ማዕከሉ ነገ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ነው ያመላክቱት።

በተመሳሳይ በድሬዳዋ አስተዳደር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነገ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሃይር ሐጂ ኑር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአስተዳደሩ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በተሰሩ ስራዎች አበረታች ለውጦች ተገኝተዋል።

ተግባራቱን በላቀ ደረጃ ለማሳደግ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነገ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል።

ድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ ተቋማት አገልግሎቶችን በተቀናጀ መንገድ በቴክኖሎጂ ታግዘው ግልፅነትና ፍጥነትን ማዕከል አድርገው እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።

የአገልግሎቱ መጀመር የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተቀናጀ መንገድ የመመለስ ጉዞን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚያስችልም አመላክተዋል።

በተመሳሳይ በሲዳማ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ነገ በይፋ ተመርቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም