ቀጥታ፡

የመስቀል በዓል በድምቀት እንዲከበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2018(ኢዜአ)፦ የመስቀል በዓል በድምቀት እንዲከበር፣ አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲጠናቀቅ እንደ ሌሎች የአደባባይ በዓላት ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብጹዕ አቡነ ዲዎስቆሮስ እንዲሁም የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ህርያቆስ እና የመስቀል በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ በተገኙበት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ከከተማው አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ጋር በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት እና በከተማው አስተዳደር በሚደረገው ድጋፍ ዙሪያ ተወያይተዋል።


 

በውይይቱ ላይም የበዓሉ ዋና ባለቤትና በዓሉን የምትመራው፤ የምታስተባብረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብትሆንም በዓሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በአደባባይ የሚያከብረው የሀገር ሀብት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የመስቀል በዓል የከተማችን ድምቀት፣ የቱሪዝም መስህብ ነው ያሉት ከንቲባዋ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን እና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ በድምቀት እንዲከበር የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ለመስቀል በዓል ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአደባባይ ክብረ በዓላት ሲከበሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ አባቶች እና የኮሚቴው አባላት የመስቀል ደመራ በዓል መስቀል አደባባይን ጨምሮ በ2 ሺህ 375 ደብሮችና ቦታዎች ላይ እንደሚከበር ጠቅሰው፤ ለከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም