አበረታች ቅመሞች በስፖርት ዘርፉ የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመከላከል ትኩረት ተደርጓል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
አበረታች ቅመሞች በስፖርት ዘርፉ የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመከላከል ትኩረት ተደርጓል - ባለስልጣኑ
አዳማ፤ መስከረም 14/2018(ኢዜአ)፦ አበረታች ቅመሞች በስፖርት ዘርፉ የሚያስከትሉትን ጉዳት በዘላቂነት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ ለስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት አመራሮችና ባለሙያዎች ያዘጋጀው የፀረ-አበረታች ቅመሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በዚህ ወቅት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል እንዳሉት ባለሥልጣኑ አበረታች ቅመሞች በስፖርት ዘርፉ የሚያስከትሉትን ጉዳት በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየሰራ ይገኛል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ለስፖርተኞች፣ ለባለሙያዎች፣ ለአመራሮችና ለባለድርሻ አካላት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም አበረታች ቅመሞችን ለመከላከል የወጡ የህግ ማዕቀፎችን ለመተግባር ተቋማዊ አቅም መገንባት ላይ መሰራቱን አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ የሰው ሀይልን የማብቃትና የአሰራር ሥርዓቶችና የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆኑን መሆኑን ገልጸዋል።
ከአበረታች ቅመሞች ነፃ የሆነ ስፖርትና ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት ሚና ወሳኝ መሆኑንና ለተግባራዊነቱ ማዕከላቱ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚሰጡት ስልጠና ላይ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ የቴክኒክ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።
የአበረታች ቅመሞች የምርመራና የቁጥጥር ስራን በማጠናከርም ባለፈው በጀት ዓመት ለ1ሺህ 96 ስፖርተኞች ምርመራ መደረጉን ተናግረዋል።
የተከለከለ አበረታች ቅመም በመጠቀም ያልተገባ ውጤት ለማስመዝገብ መጣር ወንጀል ከመሆኑ ባሻገር በሀገር ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው በመረዳት ችግሩን ለመከላከል ሁሉም በኃላፊነት ስሜት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ እንዳሉት ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ስፖርተኞች የስፖርት አበረታች ቅመሞች/ዶፒንግ/ መከላከል ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት ችግሩን ከመሠረቱ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው።
በተለይ ስፖርተኞች አበረታች ቅመሞችን መጠቀም በኢኮኖሚና በጤናቸው ላይ የሚያስከትለውን አዕምሯዊና አካላዊ ጉዳት እንዲረዱ በማስቻል ራሳቸውን ከድርጊቱ በመቆጠብ ውጤታማ ስፖርተኛ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊና የደብረ-ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ዳይሬክተር ያለው ቸኮል በበኩላቸው ማዕከሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ጎን ለጎን በቆይታቸው ስለአበረታች ቅመሞች ጉዳት ግንዛቤ እንዲኖራቸው እያደረግን ነው ብለዋል።
የዚህ ዓይነቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክም በስፖርት አበረታች ቅመሞች ምንነት፣ የህግ ጥሰቶች፣ የስፖርት አበረታች ቅመሞች ምርመራና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖረን ያደርጋል ነው ያሉት።