አብሮነትና የልማት ተሳትፎን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶች ሀገራዊ ብልጽግናን ለማፋጠን ፋይዳቸው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አብሮነትና የልማት ተሳትፎን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶች ሀገራዊ ብልጽግናን ለማፋጠን ፋይዳቸው የጎላ ነው
አርባ ምንጭ ፤ መስከረም 14/2018 (ኢዜአ)፡- የህዝብን አብሮነትና የልማት ተሳትፎ የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶች ሀገራዊ ብልጽግናን ለማፋጠን ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን በጋሞ የዘመን መለወጫ በዓል ላይ የተሳተፉ ታዳሚዎች ገለጹ።
በጋሞ ዞን ''ዮ-ማስቃላ''፣ "ቡዶ ከሶ"፣ "ባላካዳባ" የዘመን መለወጫ በዓላት "የጋራ እሴቶች ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በአርባ ምንጭ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙ ታዳሚዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የህዝብን አብሮነት፣ ልማትና ሰላም የሚያጠናክሩ እሴቶችን በመጠበቅና ማጎልበት ከተቻለ የተጀመረውን ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በአብሮነት ማጠናቀቅ እንደተቻለ ሁሉ አብሮነትን የሚያጠናክሩትን ባህላዊ እሴቶች በመጠቀም ህዝብን ለልማት ማነሳሳትና የልማት ፕሮጀክቶችን ማፋጠን እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባስኬቶ የመጡት አቶ ወንዳፍራሽ ንጉሴ እንደገለጹት በየአካባቢው የሚከበሩ የብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት ለህዝቦች አንድነትና ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ጉልህ ፋይዳ አላቸው።
ባህላዊ እሴቶቹን ይበልጥ ማጎልበት ከተቻለ መሰል ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትልቅ አቅም ይሆናሉ ብለዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የመጡት አቶ ማቲ ኦጤሳ በበኩላቸው እንዳሉት የብሔረሰቦች በዓላት የህዝብ ለህዝብ ትስስር በመፍጠር ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ለማጠናከር ያግዛሉ።
መንግስት የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የህዝቦችን አብሮነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
"ትናንት አንድ ሆነን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ገንብተን ታሪክ ጽፈናል" ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ በመደመር ሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት አብሮነትን ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ለዚህም በተለይ ህዝቡ ውስጥ ያሉ የአብሮነት እሴቶች ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በየአካባቢው የሚከበሩ የዘመን መለወጫ በዓላት ዘላቂ ሰላምና የህዝብ አንድነት ከማጠናከር አንጻር ጉልህ ፋይዳ አላቸው ያሉት ደግሞ አቶ ሞናዬ ሞሶሌ የተባሉ ታዳሚ ናቸው።
የዘመን መለወጫ በዓላት የወንድማማችነትና የእህትማማችነት መገለጫ ከመሆኑ በላይ የህዝቡን የእርስ በርስ ትስስርና የመደጋገፍ እሴት የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።
በዓላቱ ያሏቸው ባህላዊ እሴቶች የዜጎችን የሥራ ባህል፣ የሰላምና የልማት ተሳትፎ ያበረታታሉ ያሉት አቶ ሞናዬ በበዓሉ የሚታየውን የህዝቦች አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት እንተጋለን ብለዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ በትናንትናው ዕለት በተከበረው የዘመን መለወጫ በዓል ላይ የፌዴራልና የክልል የመንግስት ሥራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።