ቀጥታ፡

በዓላቱ በድምቀት እንዲከበሩ የበኩላችንን ሃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል- ወጣቶችና የሰላም ሰራዊት አባላት 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2018 (ኢዜአ)፡-የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ሀይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊታቸውን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እንዲከበሩ የበኩላቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በጎ ፈቃደኛ  ወጣቶችና የሰላም ሰራዊት አባላት ገለጹ።

ክረምት ማብቃቱን ተከትሎ ከአዲስ አመት በኋላ በአገሪቱ ከሚከበሩ ታላላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት መካከል መስቀልና ኢሬቻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በዓላቱን በተለይም በአዲስ አበባ ትውፊታቸውን በጠበቀ መልኩ ለማክበር የሚያስችሉ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

በዚህም በመዲናዋ የሚገኙ ወጣቶች በዓላቱ በተለየ ድምቀት እንዲከበሩ የበኩላቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ወጣት ኢታ ገመቹ የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቋል፡፡


 

በበዓላቱ ላይ ለመታደም ከተለያዩ አገራት የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ባህል ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት ደስታ ስዩም ነው።


 

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላምና የልማት ጉዞ ለማስቀጠል ቀን ከሌት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሶ፤ ወጣቶች ጥረቱን በትጋት ማስቀጠል አለብን ሲል ተናግሯል።

በመዲናዋ በበጎ ፈቃድ ስራዎች የተሰማራችው ወጣት ዕሌኒ ልዑል እንደገለጸችው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ማለት አቅሙን፣ ጊዜውንና  ህይወቱን ሳይሰስት ለአገሩ የሚሰራ ማለት ነው።


 

በመሆኑም የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓል ከመቼውም በላይ በደመቀ መልኩ እንዲከበር የበኩሏን ሃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀቷን ተናግራለች።


 

በዓላቱን በአብሮነት እና በአንድነት ለማክበር በሚደረገው ጥረት እንደ አንድ ወጣት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ዳዊት ጥላሁን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም