ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር መጠናከርና ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ መሠረት ነው- የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር መጠናከርና ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ መሠረት ነው- የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት የተሳካው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር መጠናከርና ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ መሠረት መሆኑን የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ።
በኢትዮጵያውያን ገንዘብ፣ የላብና የደም አሻራ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦች በማሳካት ረገድ አስተዋጽኦ ያበረክታል- ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንዳቸው ዳግማዊ ዓድዋን የደገሙበት ታሪካዊ ድል መሆኑን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል።
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ በኃይል በማስተሳሰር የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ሻሪፉል ኢስላም ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ግድቡ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን የማሳካት ትልቅ አቅም እንዳላት እንደሚያሳይም ገልጸዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ የተለያየ አስተሳሰብ፣ እምነት፣ ቋንቋና ሃይማኖት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ያሳኩት ትልቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ግድቡ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ምርታማነትን በማሳለጥ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥንና የዜጎችን ህይወት ለመቀየር መሰረት የሚጥል ከመሆኑ ባሻገር በቀጣናው ያለውን ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያሻሽላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቡሩንዲ አምባሳደር ዊሊ ኒያሚትዌ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በወኔ፣ በጋራ ጥረትና በአንድነት ያሳኩት ታላቅ ድል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የፕሮጀክት አመራር ብቃት የታየበት እንዲሁም ሀገራዊና አህጉራዊ ግብን የማሳካት ጽኑ ፍላጎታቸውን በተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙ ለአፍሪካ ትምህርት የሰጡበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ አፍሪካውያን ተባብረን በመስራት የአህጉሪቷን መጻኢ ተስፋ ብሩህ ማድረግ እንደምንችል ማረጋገጫ ቃል ኪዳን ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የናይጀሪያ ምክትል አምባሳደር ማክሲ ኦክቤዴ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው የኃይል አቅርቦት እምቅ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያና የተፋሰሱ ሀገራትን በኃይል በማስተሳሰር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ትብብርን እንደሚያጠናክርም ነው ያነሱት።
በአፍሪካ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በማሻሻል ለመሰረተ ልማት መስፋፋትና በአፍሪካውያን መካከል ትብብርን ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡