ቀጥታ፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኃይል ፍላጎት በማሟላት ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2018 (ኢዜአ)፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የአምራች ኢንዱስትሪውን የኃይል ፍላጎት በማሟላት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና አምራቾች ገለጹ።

በኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ መመረቁ ይታወቃል።

ይህም ከአምራች ኢንዱስትሪው በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረውን አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ችግር በመፍታት ኢንዱስትሪው ምርትና ምርታማነቱን የበለጠ እንዲያሳድግ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን የዘርፉ ተዋንያን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የአላላ ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ከሊፋ ሁሴን ኢንዱስትሪው ስጋና የስጋ ውጤቶችን ወደ ውጪ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ኢንዱስትሪው ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱን ተናግረዋል።

ኦማን፣ ባንግላዲሽ፣ ካምቦዲያ፣ ሲሼልስ፣ አዘርባጃንና ኮትዲቯር አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎቻቸው መሆናቸውንና በቀጣይም በቻይናና በሌሎች ሀገራት ምርቶችን መላክ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

ይሁንና ከዘላቂ የኃይል አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮች ጋር በተገናኘ ኢንዱስትሪው ሙሉ አቅሙን መጠቀም አለመቻሉን ተናግረው፥ አሁን ላይ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መመረቁ ትልቅ መፍትሔ ይዞ ይመጣል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ኢንዱስትሪው የበለጠ ሥራ ዕድል  እንዲፈጥርና የውጭ ምንዛሬ የማምጣት አቅሙን ያሳድጋል ነው ያሉት።

የቲኬ ግሩፕ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቶፊቅ ከድር በበኩላቸው ኢንዱስትሪው በልዩ ኢኮኖሚ ዞን በአጭር ጊዜ ግንባታውን አከናውኖ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል።


 

ፋብሪካው ተኪ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በስፋት ለማቅረብም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

በኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት ምክንያት አሁን ላይ በሁለት ማሽኖች ብቻ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው፥ የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግሩን በዘላቂነት እንደሚፈታ ገልጸዋል።

እንደ ሀገር ካለው ኃይል የማመንጨት አቅም አኳያ በርካታ ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም የተመረተውን ኃይል በአግባቡ ማዳረስ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ያነሱት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ናቸው።


 

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኃይል አቅርቦት በእጥፍ በማሳደግ የፋብሪካዎችን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል ብለዋል።

አሁን ላይ ኢንዱስትሪው በሚፈልገው ልክ ኃይል ለማቅረብ የማሰራጫና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራ ደረጃ በደረጃ እንደሚተገበር አመልክተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንደሚሉት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዋነኛ ማነቆ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አለመኖር አንዱ ሲሆን፥ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።


 

የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በቂ የኃይል አቅርቦትን በመፍጠር የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አጠቃቀም ያሳድጋል ነው ያሉት።

የአምራች ኢንዱስትሪውን አዳጊ የኃይል ፍላጎት የማሟላት ሥራም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን በየጊዜው ምላሽ ይሰጣል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም