ቀጥታ፡

የመስቀል በዓልን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን እና  ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ተዘጋጅተናል- የሃይማኖት አባቶች 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2018 (ኢዜአ)፡- የመስቀል በዓልን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱንና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ የዓለም አስደናቂ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።


 

የበዓሉን ሃይማኖታዊ ትውፊት በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች በኢትዮጵያ የሚከበረው የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እና እሴት ከሌላው ዓለም ልዩ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የካራቆሬ መዝገበ ምሕረት ቅዱስ ፋኑኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ መልዓከ ኃይል አባ አማኑኤል፤ የመስቀል በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅርን ጥግ ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡


 

የመስቀል በዓል ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ለማግኘት በትንቢትና በደመራ ጭስ በመመራት መስቀሉ ከተቀበረበት ቆሻሻ ስፍራ የተገኘበት ዕለት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር የቤተክርስቲያን ሊቃውንትና መዘምራን በሚያሰሙት የቅዱስ ያሬድ ዜማ፣ በሚያሳዩት ትርዒትና በምዕመናን ባህላዊና ሃይማኖታዊ  አለባበስ መታጀቡ ልዩ ድምቀት እንዲኖረው ማስቻሉን ገልጸዋል ፡፡

የየካ አባዶ ደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን አገልጋይ መልዓከ ሰላም ገብረመስቀል ዳምጠው በበኩላቸው የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱንና ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት የሚከበር የዓለም ቅርስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ስርዓቱ በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች የተራራቁ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚገናኙበት፣ ዘመድ የሚጠያየቅበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት እንዲሁም አብሮነትና አንድነትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱንና ትውፊቱን ሳይለቅ ለትውልድ እንዲተላለፍ የበዓሉ እሴት የሆኑ አለባበሶች፣ ቁሳቁሶችና ልዩ ልዩ የአከባበር ትውፊቶቹን መጠበቅና ማልማት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም