ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካ በዓለም መድረክ ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራት ድጋፉን ሊሰጥ ይገባል- አምባሳደር ሳልማ ማሊካ ሃዳዲ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2018(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካ በዓለም መድረክ ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራት እያደረገችው ላለው ጥረት ድጋፍ እንዲሰጥ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሳልማ ማሊካ ሃዳዲ ጥሪ አቀረቡ።

80ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ በድርጅቱ ዋና መቀመጫ ኒውዮርክ እየተካሄደ ይገኛል።

የጠቅላላ ጉባኤው አካል የሆነ ከፍተኛ የምክክር እና ክርክር መድረክ ዛሬ በኒው ዮርክ ተጀምሯል።

“'ደህናነት በአብሮነት፤ 80 ዓመታት እና ከዚያ በላይ ለሰላም፣ ለልማት እና ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው ጉባኤው የሚካሄደው።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሳልማ ማሊካ ሃዳዲ “እየተለወጠ ባለው የዓለም የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ የአፍሪካ ምልከታዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ለጉባኤው ተሳታፊዎች የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አምባሳደር ሳልማ በመልዕክታቸው አፍሪካ በተለያዩ መስኮች ራሷን ለመቻል እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎች ፍሬ እያፈሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አፍሪካ የደህንነት ጉዳዮች በራሷ ፋይናንስ በማድረግ ረገድ ለውጥ ማምጣቷን በማሳያነት ጠቅሰው የአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ማዕቀፍ በአፍሪካውያን ገንዘብ እና ባለቤትነት እየተመራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ በአፍሪካውያን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በትግበራ ላይ መሆኑን አንስተዋል።

አምባሳደሯ በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ላይ ያላቸውን ሀሳብ ያጋሩ ሲሆን የንግድ ቀጣናው ዜጎች እና ገበያን ከማስተሳሰር ባለፈ ሰው ሰራሽ ድንበሮች በእኛ ላይ ከመጫናቸው በፊት የነበረውን የንግድ ትስስር እና ትብብር እንደሚመለስ ተናግረዋል።

አፍሪካ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ያላት ድርሻ እያደገ መምጣቱን ገልጸው አህጉሪቷ በቡድን 20 ቋሚ መቀመጫ ማግኘቷ አበይት ማሳያ ነው ብለዋል።

አፍሪካ በቡድን 20 ውስጥ ያገኘችው ቋሚ መቀመጫ ለዓለም ችግሮች መፍትሄ ያላትን አይተኬ ሚና በግልጽ የሚያመላክት እንደሆነም ተናግረዋል።

እየተለወጠ ያለው የዓለም ስርዓት ለአፍሪካ በርካታ እድሎችን ይዞ መጥቷል ያሉት ምክትል ሊቀመንበሯ ይህን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አምባሳደር ማሊካ ዓለም አቀፍ አጋሮች አፍሪካ የዓለም የፋይናንስ ስርዓት እኩልነት የሰፈነበት እንዲሆን እና በተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት ውክልና እንድታገኝ እያነሳች ያለው ፍትሃዊ ጥያቄ እና እውነተኛ መሻት እንዲደግፍ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

አፍሪካ ከዓለም ጋር ያላት ትብብር በጋራ መከባበር እና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው አፍሪካ ስታድግ የዓለም ብልጽግና እና መረጋጋት ይረጋገጣል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም