ሕዳሴ ግድብ በቀጣናው የጋራ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ድንበር ተሻጋሪ ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሕዳሴ ግድብ በቀጣናው የጋራ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ድንበር ተሻጋሪ ፕሮጀክት ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2018 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድንበር ሳይገድበው ቀጣናዊ የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ የፓን አፍሪካ ትብብር ማሳያ መሆኑን የሲቢኢ ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም መመረቁ የሚታወስ ነው።
ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች ባለፈ ለቀጣናው ሀገራት እና ለአፍሪካ አህጉር ኢኮኖሚ የምስራች ይዞ የመጣ ነው።
አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ሕዳሴ ግድብ የፓን አፍሪካ ትብብር ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የግድቡ ስኬት ልማቶች የፖለቲካ ድንበር ሳይገድባቸው የጋራ የኢኮኖሚ ትሩፋቶችን ማምጣት እንደሚችል ተምሳሌት የሆነ ፕሮጀክት መሆኑን አመልክተዋል።
ሕዳሴ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ የጠለቀ ጠቀሜታ አለው ያሉት አቶ ዘመዴነህ አንድምታው የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ያለፈ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአፍሪካ ትልቁ እና በዓለም ላይ ከሚገኙ 10 የኃይል ማመንጫ ግድቦች አንዱ የሆነው የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የማሳካት የጋራ ፍላጎት እና አቅምን እንደሚያሳይም ነው የገለጹት።
የሕዳሴ ስኬት የብሄራዊ ኩራት ምንጭ ነው ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ያለ ውጭ እርዳታ ማሳካት አይቻልም የሚለውን እሳቤ ፉርሽ ማድረጉን አመልክተዋል።
አቶ ዘመዴነህ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የኃይል ማመንጨት አቅም በማሳደግ በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አምራች ሀገራት አንዷ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጠን መጨመር የኢንዱስትሪ እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን በማነቃቃት የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚወጣም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ዝቅተኛ የኤሌትሪክ ኃይል ክፍያ ያላት ሀገር መሆኗ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሳብ እንደሚያስችላትም ነው ያብራሩት።
በአፍሪካ ለማኑፋክቸሪንግ እድገት ሳንካ የሆነው አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ የኃይል አቅርቦት አለመኖር መሆኑን የገለጹት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ሕዳሴ ግድብ ከዚህ አንጻር ለኢትዮጵያ ተነጻጻሪ ጠቀሜታ እንደሚሰጣት ገልጸዋል።
ግድቡ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር አቀጣጣይ ሞተር እንደሆነም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምትሸጠው የኤሌክትሪክ ኃይል የቀጣናው አንድነት እና ትብብር የበለጠ እንደሚያጎለብትም አክለዋል።