ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት የሀገር በቀል የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀሟ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት የሀገር በቀል የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀሟ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2018(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ስራዎቿ የሀገር በቀል የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀሟ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ተግባር መሆኑን ግሎባል ግሪን ግሮውዝ ኢኒስቲትዩት የተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም አስታወቀ።
ኢኒስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ አረንጓዴ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልም ገልጿል።
ግሎባል ግሪን ግሮውዝ ኢኒስቲትዩት እ.አ.አ በ2012 የተቋቋመ ዓለም አቀፍ የበይነ መንግስታት ተቋም ሲሆን በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት አረንጓዴ እና ዘላቂ እድገትን እንዲያረጋግጡ ድጋፍ ያደርጋል።
ኢኒስቲትዩቱ በዓለም ዙሪያ 52 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪካ ሀገራትን አካቷል።
የግሎባል ግሪን ግሮውዝ ኢኒስቲትዩት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ካትሪና ሲንግላኪስ ኢኒስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ጋር በአረንጓዴ እድገት እና ልማት በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራ ከ10 ዓመት በላይ ድጋፍ ማድረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በስትራቴጂው አማካኝነት በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን ገልጸው የተራቆቱ መሬቶች መልሰው ማገገም እና በመላው ኢትዮጵያ የተካሄዱ የችግኝ ተከላ ስራዎችን ያመጡትን ውጤት በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኢንስቲትዩቱ በስትራቴጂው ቀረጻ እና ትግበራ፣ የአቅም ግንባታ እና ስትራቴጂውን ለሚተገብሩ ተቋማት የቴክኒክ ድጋፎችን ማድረጉን አመለክተዋል።
የታዳሽ ኃይል ልማት፣ በጥምር ደን ግብርና (አግሮ ፎረስትሪ) እንዲሁም የግብርና ምርታማነት ማሳደግ ስራን ከአይበገሬ አቅም ግንባታ እና የበካይ ጋዝ ቅነሳ ጋር በማስተሳሰር ለሚከናወኑ ስራዎች ድጋፍ መስጠቱን ነው ዳይሬክተሯ ያብራሩት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና አመራር ሰጪነቱ ለውጤታማነቱ ወሳኝ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የራሷን የፋይናንስ እና የሰው ሀብት አቅም ከአጋሮች የቴክኒክ ድጋፎች በማጣመር ያከናወነችው ስራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።
ለአረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የፋይናንስ አማራጮችን መጠቀሟ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚያስችሏትን ኢኒሼቲቮች እየተገበረች መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ ሀገር በቀል የፋይናንስ ሀብቶችን በመጠቀም አርንጓዴ እድገት ለማምጣት እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ስራዎች ማህበረሰቡን በንቃት ማሳተፏ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል ነው የገለጹት።
በተለይም የወጣቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣት ለአረንጓዴ እድገት እና ዘላቂ ልማት ያለው አበርክቶ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያን መጪ ጊዜ የተሻለ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ግሎባል ግሪን ግሮውዝ ኢኒስቲትዩት ኢትዮጵያን ጨምሮ አረንጓዴ ሽግግር እያደረጉ ለሚገኙ የአፍሪካ እና በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።