ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብን ለመገንባት አብረን በመቆማችን ተጠናቆ ደስታችንን ለመግለፅ በቅተናል - የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች 

ሀዋሳ ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለመገንባት አብረን በመቆማችን ተጠናቆ አብረን ደስታችንን ለመግለፅ በቅተናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ ፡፡

በሀዋሳ ከተማ የተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተሳታፊዎች "የህዳሴው ግድብን ለመገንባት አብረን በመቆማችን፤ በመጠናቀቁ ደግሞ አብረን ደስታችንን ለመግለፅ በቅተናል" ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሁባ ጀማል ኢትዮጵያውያን የህዳሴው ግድብ ጅማሮ ከተበሰረበት ዕለት አንስቶ በጋራ በመቆማቸው የግድቡ መጠናቀቅ እውን ሊሆን መቻሉን ተናግረዋል።


 

የዎንሾ ወረዳ ነዋሪው አቶ ደስታ ሙኩካ በበኩላቸው አንድ ሆነን በመስራታችን የጀመርነውን እንደጨረስነው ሁሉ በቀጣይ ሌሎች ፕሮጀክቶችም ስኬታማ እንዲሆኑ የበኩላችንን  እንወጣለን ብለዋል።


 

በሲዳማ ክልል የቀድሞ ጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሰራዊት ማህበራት ህብረት አባል የሆኑት ሀምሳ አለቃ ዳንኤል ሀብተወልድ ለ25 ዓመታት በውትድርና ሙያ ሀገራቸውን ማገልገላቸውን ጠቅሰው የግድቡ መጠናቀቅ ሁሌም ለሀገሩ ለመሰዋት ዝግጁ ለሆነ ወታደር የሚፈጥረው ስሜት የተለየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፤ የህዳሴው ግድብ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ያለፈ ዘርፈ ብዙ ተምሳሌትነት ያለው እንደሆነ ጠቅሰው የኢትዮጵያ ክብርና ኩራት ምንጭም ነው ብለዋል ፡፡


 

ከዚህ በኋላም እንደ ሀገር የምንፈልጋቸውን ጉዳዮች በራሳችን አቅም ማሳካት እንደምንችል የግድቡ መጠናቀቅ ማረጋገጫ ሆኖልናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ትልቅ የዲፕሎማሲ አቅምም የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

በህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ መኮንኖችና አባላት እንዲሁም ከሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም