ቀጥታ፡

የዘመን መለወጫ በዓላት እሴቶች ለአብሮነትና ሰላም ግንባታ መጠናከር የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው - ርዕሰ መስተዳድር  ጥላሁን ከበደ

አርባ ምንጭ፤ መስከረም 13/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚከበሩ የዘመን መለወጫ በዓላት እሴቶች ለአብሮነትና ሰላም ግንባታ መጠናከር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

በክልሉ የጋሞ  "ዮ-ማስቃላ፣ የዘይሴ  "ቡዶኬሶ " እና የጊድቾ "ባላካዳቤ" የዘመን መለወጫ በዓላት በአርባ ምንጭ ከተማ በመከበር ላይ ናቸው። 


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት  የክልሉ  ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤  በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩ የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓላት እሴቶች ለአብሮነት፣ ለአንድነትና  ለሰላም ግንባታ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ  አላቸው።

ከእነዚህ መካከል የጋሞ፣ የዘይሴና የግድቾ የዘመን መለወጫ በዓላት እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ የበዓላቱ እሴቶች ሕብረተሰቡ ተከባብሮና ተዋዶ ለዘመናት በአብሮነትና በሰላም እንዲኖር ማድረጋቸውን አንስተዋል።

የዘመን መለወጫ በዓላቱ  የአንድነት፣  የአብሮነትና የብዝሃነት ማሳያ ናቸው  ብለዋል።

ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እውን በማድረግ የጋራ ታሪክ በተመዘገበበት ማግስት የዘመን መለወጫ በዓላቱ መከበራቸው የተለየ ደስታ መፍጠራቸውንም ጠቅሰዋል።


 

የክልሉን ህዝብ በማስተባበርና አንድነቱን በማስጠበቅ ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በተደረገው ጥረት ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ ያሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በተደረጉ ጥረቶችም ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ ሕዝቡ የክልሉን ሁለንተናዊ ብልጽግና  ለማረጋገጥ  በሚከናወኑ ተግባራት  የበኩሉን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) ፤  ለጋሞ "ዮ-ማስቃላ፣  ለዘይሴ " ቡዶኬሶ"  እና  ለግድቾ " ባላካዳቤ" በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

ባህላዊ እሴቶችን በማጎልበት አብሮነትን  አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በዓሉ ከዘመን መለወጫነት ባለፈ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የእርቅና የሰላም እንዲሁም የሕዝቡ ባህል፣ ወግና እሴት ይበልጥ የሚጎላበት ነው ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) ናቸው።


 

የዘመን መለወጫ በዓላቱ  ከዓመት ወደ ዓመት የተሸጋገርንበት የምስጋና በዓል ከመሆናቸው ባሻገር ለኢኮኖሚ ፣ ለሰላም ግንባታና  ለብልጽግና ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር  የስራ ኃላፊዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የማሕበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም