ለአምራች ኢንዱስትሪው የተሰጠው ትኩረት የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በአገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ለአምራች ኢንዱስትሪው የተሰጠው ትኩረት የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በአገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱ አስችሏል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠው ልዩ ትኩረት የመድሃኒት እና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በአገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱ ማስቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢትዮጵያ መድሃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ዘርፍ ማህበር ከጤና ሚኒስቴር እና ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር 22ኛውን ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት፣ መንግስት የአገርን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል አንዱ የጤና ዘርፍ ነው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ አመታት ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘርፉን ለመደገፍ የመብራትና የመንገድ መሰረተ ልማቶች መዘርጋታቸውን፣ ቀደም ሲል የነበሩ ህጎች፣ ፖሊሲዎች እንዲሁም የአገር ውስጥ ምርት ግዥ መመሪያዎች መሻሻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የመድሃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ ገቢ ምርቶችን በመተካት ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ መመዝገቡን ጠቁመዋል።
በ2017 በጀት አመት መጨረሻ አካባቢ ብቻ በኢንዱስትሪ ዘርፉ 4 ነጥብ 53 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ልዩ ልዩ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የመድሃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግብዓት ትልቅ ድርሻ እንደሚይዝ ጠቅሰው ለተገኘው ውጤት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውቀዋል።
በቀጣይ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው በማሳሰብ መንግስት የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት መድሃኒቶችንና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በአገር ውስጥ ማምረት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የጤና ቱሪዝም ማዕከል ትሆናለች ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፤ ለዚህም እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦት ትልቅ ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድሃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራች ዘርፍ ማህበር ፕሬዚዳንት ዳንኤል ዋክቶሊ (ዶ/ር) ባለፉት ጥቂት አመታት መድሃኒቶችንና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በአገር ውስጥ በማምረት ረገድ አበረታች ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
በዚህም መድሃኒት በማምረት ስምንት በመቶ የነበረው የአገር ውስጥ ምርት የገበያ ድርሻ አሁን ላይ ወደ 41 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
ለተገኘው ለውጥ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረትና የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፋርማሲቲካል ዘርፍ ከፍተኛ አቅም እና እድል አላት ያሉት ደግሞ በአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሱዳንና የኤርትራ የሰው ሃብት ልማት መሪ ሸሪን ቫርኪን (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የአለም ባንክ ለዘርፉ ዕድገት የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጠልም አረጋግጠዋል፡፡