የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ)፦ የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።
ቢሮው በመስከረም ወር የሚከበሩ የአደባባይ በዓላትን አስመልክቶ ከሴቶች ማህበራት ጋር ውይይት አካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ እንዳሉት፤ የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ሃይማኖታዊ እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
አዲስ አበባ የህብረ ብሔራዊነትና የአንድነትን መገለጫ ተምሳሌት መሆኗን ጠቅሰው፤ ሴቶች በሰላምና በልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዓላቱን ለማክበር ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን ቆይታ ያማረ ለማድረግ የሴቶች ተሳትፎ ከመቼውም በላይ ጎልቶ መውጣት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
በዓላቱ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ ማሳደግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ እናትዓለም እንዳለ በበኩላቸው፤ በአዲሱ ዓመት የሚከበሩ በዓላት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቅ ማግስት የሚከበሩ በመሆኑ ለኢትዮጵያዊያን ድርብ በዓላት ናቸው ብለዋል።
የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላትን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊታቸውን ሳይለቁ እንዲከበሩ ለማስቻል ሴቶች ተሳትፏቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
የማኅበሩ አባል የሆኑት ወይዘሮ ብርሃኔ ዘውዴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የብሄር ብሄረሰቦችን አንድነትና ጥምረት የሚያሳዩ ናቸው።
በዓላቱ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊታቸውን ሳይለቁ አንድነትን በሚያጎላ ሁኔታ እንዲከበሩ ከጸጥታ አካላት ጋር በጥምረት ለመስራት ተዘጋጅተናል ብለዋል።