ቀጥታ፡

በህዋ ምርምር ተግባራዊ እውቀትን እና የምርምር ክህሎትን ለማሳደግ ታዳጊ ተማሪዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በህዋ ምርምር ላይ ተግባራዊ እውቀትን እና የምርምር ክህሎትን ለማሳደግ ታዳጊ ተማሪዎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ከፊቸር አፍሪካ ስፔስ ኤክስፕሎሬሽን ስቲም አካዳሚ እና ከቦይንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር በመሰረታዊ የህዋ ሳይንስ ዙሪያ ያሰለጠናቸውን 109 ታዳጊ ኢትዮጵያውያንን አስመርቋል። 


 

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቤተልሔም ንጉሴ በዚሁ ወቅት እደገለጹት  ኢንስቲትዩቱ በህዋ ምርምር ተግባራዊ እውቀትንና የምርምር ክህሎትን ለማሳደግ ታዳጊ ተማሪዎች ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።

ይህም ታዳጊዎች በህዋ ሳይንስ መሠረታዊ የሆነ ክህሎት እና እውቀት እንዲጨብጡ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት አምስት ወራት 109 ተማሪዎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምናባዊ እውነታ (virtual reality) እና የምስለ በረራ (virtual flight) ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚህም መንኮራኩርን መቆጣጠር፣ በህዋ ላይ ጉዞ ማድረግ፣ የህዋ ላይ መጓጓዣዎችን ማሳረፍን የተመለከተ ሥልጠና ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ሥልጠናው ለወደፊት እንደሀገር በህዋ ሳይንስ ዙርያ የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የቦይንግ ኢትዮጵያ የፕሮግራም ዳይሬክተር ዘመነ ነጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ለስፔስ ሳይንስ ትኩረት መስጠታቸውን ተናግረዋል።


 

ቦይንግ ኩባንያ ይህንኑ እንቅስቃሴ ለመደገፍና በዘርፉ የሚፈለገውን የሰው ኃይል ለማፍራት በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።  

ኩባንያው ሀገራቱ በስፔስ ዙሪያ በሚያደርጓቸው ምርምሮች እና እንቅስቃሴዎች የራሱን አስተዋፅኦ ለማድረግ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

የፊቸር አፍሪካ ስፔስ ኤክስፕሎሬሽን ስቲም አካዳሚ መስራችና ዋና ዳይሬክተር ሴን ጃኮብስ በበኩላቸው በአፍሪካ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት ለመደገፍ የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።


 

አካዳሚው የአፍሪካ ተማሪዎች በህዋ ሳይንስ እና ፈጠራ መሪ ሆነው የሚወጡበትን ጊዜ እውን ለማድረግ ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

ስልጠናቸውን አጠናቀው የተመረቁት ህማን ሰይድ እና ኦሊያድ ደጀኔ በስልጠናው በህዋ ሳይንስ መሰረታዊ ክህሎት የጨበጡበትን ክህሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም