ቀጥታ፡

ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው የጋራ ሀብቶቻችንን ልንጠብቃቸውና ልንንከባከባቸው ይገባል- ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

ቦንጋ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ)፦ የካፈቾ የአዲስ ዘመን መለወጫ "ማሽቃሮ"ን የመሳሰሉ  ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው የጋራ ሀብቶችና ዕሴቶችን ልንጠብቃቸውና ልንንከባከባቸው ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መሰተዳደር  ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለፁ።

የ2018 ዓ.ም የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓል "ማሽቃሮ" በቦንጋ ከተማ ''ቦንጌ ሻምበቶ'' በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ተከብሯል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሰተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ "ማሽቃሮ"ን የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ባህሎቻችን የጋራ ሀብታችን በመሆናቸው ልንጠብቃቸውና ልንንከባከባቸው ይገባል ብለዋል። 

እነዚህ ባህሎችና ታሪኮች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ ምሁራንና የታሪክ አዋቂዎች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፣ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማትም አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

"የዘንድሮው የካፈቾ የአዲስ ዘመን መለወጫና የተስፋ ብስራት የሆነው "ማሽቃሮ" የአይቻልም መንፈስን የሰበርንበትና የዘመናት ቁጭት የሆነውን አባይን በመገደብ አጠናቀን ለጥቅም ባበቃንበት ማግስት የሚከበር በመሆኑ ለየት ያደርገዋል" ብለዋል።


 

"ማሽቃሮ" ካፋዎች አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ዓመት በሰላም፣ በፍቅር፣ በይቅርታና በአንድነት የሚቀበሉበት በዓል መሆኑን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዓሉ የህዝብን ትስስር የመጠበቅ መሰረትና ታሪካዊ ዳራ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የበርካታ ባህልና ታሪክ ባለቤት የሆኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገኛ ናት ብለዋል።


 

ከነዚህ ባህሎች መካከል በየአካባቢው የሚከበሩ የብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት የይቅርታ፣ የአብሮነትና አንድነት በዓላት በመሆናቸው ለሀገር ሰላም የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል። 

የካፋ ህዝብ የበርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ቱባ እሴቶች መገኛ ነው ያሉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፣ እሴቶቹ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ መደረጉ ለልማትና ለሰላም ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።


 

የዘንድሮ ማሽቃሮ ከቀበሌ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን ያነሱት አቶ እንዳሻው፣ በዛሬው እለት ቦንጌ ሸምበቶ በድምቀት በመከበሩ እንኳን ደስ ያላቸሁ፣ እንኳን አደረሳቸሁ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታና የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ የስራ ኃላፊዎች፣ እንግዶችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም