ቀጥታ፡

በሰላምና ልማት ግንባታ ሂደት ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው - ምክር ቤቱ

ጅግጅጋ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ)፦ በሰላምና ልማት ግንባታ ሂደት ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ገለጸ።

"ወጣትነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ የወጣቶች ሰላምና ደህንነት ኮንፍረንስ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረገው የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና፤ በሰላምና ልማት ግንባታ ሂደት ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጿል።

የወጣቶች የሰላም ጥረትና የልማት አቅም ትርጉም ያለው ውጤት የሚያመጣ በመሆኑ በሁሉም ረገድ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።

የሶማሌ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ መሀመድ ማህዲ፤ ወጣቶች በሠላም እና የልማት ግንባታ ስራዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ ለሀገር ቀናኢነታቸውን አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፤ ማህበራዊ ልማት፤ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የወጣቶች ሰላምና ደህንነት ኮንፍረንሱ በየዓመቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 21 የሚከበረውን የዓለም ሠላም ቀን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም