ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም፣ ክብርና ሉአላዊነት የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዘጋጅተናል- ተመራቂ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም፣ ክብርና ሉአላዊነት የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዘጋጅተናል- ተመራቂ መኮንኖች
ድሬዳዋ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም፣ ክብርና ሉአላዊነት የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀታቸውን የሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተመራቂ መኮንኖች ገለጹ።
የሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን መኮንኖች የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተገኙበት መስከረም 11 ቀን 2018 ዓ.ም ማስመረቁ ይታወቃል።
ፊልድ ማርሻሉ ለተመራቂዎቹ የስራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን የሀገርን ህልውና እና ብሔራዊ ጥቅሞች ለመጠበቅ ሠራዊቱ ከምንግዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂ መኮንኖች በስልጠናው የቀሰሙት ዕውቀት አስቀድመው ከነበራቸው ልምድ ጋር በመታገዝ የትኛውንም ግዳጅ መወጣት የሚያስችል አቅም ያካበቱበት መሆኑን ገልጸዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ምክትል መቶ አለቃ መርሻ አበበ፤ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም፣ ክብር ሉአላዊነት መጠበቅ የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ሌላኛዋ ተመራቂ ምክትል መቶ አለቃ ጀማነሽ ግርማ፤ ለሀገራችን ክብርና ሉአላዊነት በጀግንነትና በቆራጥነት ለመቆም የወጣንበት ዓላማ በመሆኑ ሁሌም ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሰራዊት በዓለም አደባባይ ያለውን ጀግንነት፣ ክብርና ዝና በማስጠበቅ ከራስ አልፎ ለሌሎችም ሀገራት የሰላም ማስከበር ተምሳሌትነታችን ይቀጥላል ያሉት ደግሞ ምክትል መቶ አለቃ ማቲዎስ በቀለ ናቸው።
ምክትል መቶ አለቃ አረጋ ከተማ በበኩላቸው በቀሰሙት ወታደራዊ ጥበብና ዕውቀት በየትኛውም ግዳጅ ላይ በላቀ አፈፃፀም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የሀገርን አስተማማኝ ደህንነትና ሉአላዊነት ለማስከበር ተዘጋጅተናል በማለት የተናገሩት ደግሞ ምክትል መቶ አለቃ እርጥብነሽ ወርጋሙ ናቸው።
ምክትል መቶ አለቃ ባዩሽ እንግዳሸት በበኩላቸው ሴት ማለት ሀገር ናትና የሀገሬን ሉዓላዊነት በቁርጠኝነት ለማስከበር ዝግጁ ነኝ ሲሉ ተናግረዋል።