ቀጥታ፡

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት የተደረገባቸው ዘርፎች የተሻለ የምጣኔ ሃብት ዕድገት እንዲመዘገብ ዕድል ፈጥረዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ)፦ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት የተደረገባቸው ዘርፎች የተሻለ የምጣኔ ሃብት ዕድገት እንዲመዘገብ ዕድል መፍጠራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ ገለጹ።

አምባሳደር ግርማ ብሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተግባራዊ ማድረጓ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን አስገኝቶላታል።

በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ጨምሮ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሃብቶች ሰፊ ዕድል ይዞ መምጣቱን አንስተዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ ዋጋ እንዲወሰን መደረጉ ኤክስፖርትን ከማበረታታት ባሻገር ነጋዴው ትርፋማ እንዲሆን ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

በተለይም ከውጭ ይገባ የነበረውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ዕድገት በጥቂት ዘርፎች ላይ የተንጠለጠለ እንደነበር አስታውሰው ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ለብዝሃ ዘርፍ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ትኩረት የተደረገባቸው ዘርፎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑና ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሃብት ዕድገት እንዲመዘገብ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም