ቀጥታ፡

ለህዳሴው ግድብ ውጤት መብቃት በቦንድ ግዥ አሻራዬን በማኖሬ ተደስቻለሁ

ድሬዳዋ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ለውጤት መብቃት በቦንድ  ግዥ  አሻራውን በማኖሩ መደሰቱን  ወጣት አዲሱ ብርሃን ተናገረ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ የድሬደዋ ነዋሪዎች ደማቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወሳል።


 

በድሬዳዋ በተካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ  የህዳሴ ግድብ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተካፈለው አካል ጉዳተኛ  ወጣት  አዲሱ ብርሃን ከተሰማራበት የዶሮ እርባታ እንቁላል በመሸጥ በቦንድ ግዥ የዜግነት ሀላፊነቱን በመወጣት ተሳትፏል።

ይህ አበርክቶው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ጋር ተዳምሮ ግድቡ ለውጤት እንዲበቃ የራሱን ጠጠር በማበርከቱ ደስታና ኩራቱ ወሰን እንደሌለው  ያስረዳል።

ለግድቡ መሠረት ከተጣለበት ወቅት ጀምሮ ከሚያረባቸው ዶሮዎች የሚያገኘውን እንቁላል በመሸጥ ለተከታታይ ዓመታት ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንስቷል።

ያ ተስፋው በተደመረ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ተሳክቶ በማየቱ ደስታው ወሰን እንደሌለው ገልፆ፤ ግድቡ የሀገራችን ብርሃን ብቻ ሳይሆን ለእሱ እና ለመሰሎቹ አካል ጉዳተኞች ትልቅ ተስፋና የለውጥ መንገድ መሆኑን ተናግሯል።

በቀጣይም መንግስት ለሀገርና ለዜጎች ሁለንተናዊ ለውጥ የጀመራቸው ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ የድርሻውን እንደሚወጣ በመግለፅ።


 

ሌላው በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉት አቶ መገርሳ ነገራ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ሌሎችን ሀገራዊም ሆነ የአስተዳደሩን ፕሮጀክቶች ለማሳካት እንደሚተጉ መነቃቃት ፈጥሮላቸዋል።

የበለፀገች ሀገርን ለትውልድ ለማስረከብ መንግስት የሚቀይሳቸውን ውጥኖች ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚተጉም አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተጓዝን የትኛውንም አገራዊ ጉዳይ ከዳር ማድረስ እንደምንችል በህዳሴው ግድብ አስመስክረናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ኮውሰን መሐመድ ናቸው ።


 

ይሄን መነቃቃትና አንድነት ይበልጥ በማጠናከር በድሬዳዋ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም