ቀጥታ፡

ህዳሴ ግድብ ለአፍሪካ አይን ገላጭ ፕሮጀክት ነው - ኬንያውያን ጋዜጠኞች 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አፍሪካ ራሷን የመቻል ትልሟ እንደሚሳካ ያሳየ አይን ገላጭ ፕሮጀክት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ኬንያውያን ጋዜጠኞች ገለጹ።

አፍሪካውያን ከውጭ ጥገኝነት ተላቀው የራሳቸውን ፕሮጀክቶች በራሳቸው አቅም መገንባት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መመረቁ ይታወቃል። 

ግድቡ ከብሄራዊ ፕሮጀክትነት ባለፈ የአፍሪካን የመቻልና የማድረግ አቅም እንደሚያሳይ በስፋት እየተነሳ ይገኛል።


 

 ኬንያዊው ጋዜጠኛ ጆን ሪያጋ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአጠቃላይ ቀጣናው ታሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ያሳካችው ድል ትልቅ ነው ያለው ጆን ግድቡ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ውሃን ጨምሮ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብቶች ተጠቅመው መልማት እንደሚችሉ አይናቸውን እንዲገልጡ የሚያደርግ ነው ብሏል።

የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ፈለግ በመከተል የተፈጥሮ ሀብታቸውን ማልማትና መሰል ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚገባቸውም ተናግሯል። 

ግድቡ ከኃይል ማመንጫነቱ ባለፈ ለአፍሪካ ሰፊ የልማት አጀንዳ እንደ አሻራነት የሚያገለግል ፕሮጀክት ነው ሲልም ገልጿል።

የአፍሪካ መሪዎች አህጉሪቱ የታደለችውን ጸጋ አውጥታ በመጠቀም የልማት ትልሞቿን እንድታሳካ አበክረው መስራት እንዳለባቸውና አፍሪካውያን ተጨባጭ ውጤቶችን እንዲያገኙ በር እንደሚከፍት ነው ያመለከተው።


 

ሌላኛዋ ኬንያዊት ጋዜጠኛ አጋታ ንጎቶ የሪያጋን ሀሳብ ተጋርታ አፍሪካውያን በራሳቸው የማድረግ አቅም ሊተማመኑ ይገባል ብላለች።

ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ያለ ምንም የውጭ እርዳታ ገንብታለች፣ አፍሪካውያን ከጥገኝነት በመላቀቅ የራሳቸውን ፕሮጀክቶች በራሳቸው የፋይናንስ አቅም መገንባት ይኖርባቸዋል ብላለች።

እኛ አፍሪካውያን በራሳችን ላይ ያለንን እምነት በማጠንከር አህጉራችንን መለወጥ ይገባናል ስትልም ገልጻለች። 

ጋዜጠኞቹ ታላቁ የኢትይጵያ ህዳሴ ግድብ ከግድብ ባለፈ የአፍሪካ አይበገሬነት ተምሳሌትና ራስን በመቻል መልማት እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ፕሮጀክት እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም