ቀጥታ፡

የ"ዱቡሻ" ሥርአት አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባትና ሰላምን ለማጽናት ትልቅ አቅም በመሆኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሰራል-የባህልና ስፖርት ሚኒስትር

አርባ ምንጭ፤መስከረም 12/2018 (ኢዜአ)፡- የጋሞ ባህላዊ ሸንጎ የሆነው የ"ዱቡሻ" ሥርአት አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባትና ሰላምን ለማጽናት ትልቅ አቅም በመሆኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር  ሸዊት ሻንካ ገለጹ።  

የ"ዱቡሻ" ሥርአትን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑም ተመላክቷል።

"ዱቡሻና የዱቡሻ ወግ ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ የጋሞ የዘመን መለወጫ በዓል አውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።


 

በአውደጥናቱ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር  ሸዊት ሻንካ ኢትዮጵያ ብዝሃ ህዝብና ማንነት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ የሀገር ሰላምና ልማትን በዘላቂነት ለማጠናከር አስተዋጽኦ ያላቸው ባህላዊ እሴቶች በስፋት እንዳሉም ተናግረዋል።

የጋሞ ባህላዊ ሸንጎ የሆነው የዱቡሻ ስርአት ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጎልበት አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባትና ሰላምን ለማጽናት ትልቅ አቅም በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስቴሩ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው "የዱቡሻ ሥርአት ዘመናዊ ህግ ሳይወጣ ለህዝቦች ፍትህና ሰላም ለመስጠት ያስቻለ የቆየ ሀገር በቀል ዕውቀት ነው" ብለዋል።


 

ሥርአቱ በዘመናዊ የፍትህ ሥርአት ላይ ያለውን የሥራ ጫና በመቀነስ በኩል ፋይዳው ጉልህ በመሆኑ የዓለም የጋራ ሀብት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

የዱቡሻ ሥርአት በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጎልቶ በሚወጣበት መንገድ ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ "ሥርአቱን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት  የክልሉ መንግስት የበኩሉን ይወጣል" ሲሉ ተናግረዋል።

የጋሞ ባህላዊ ሸንጎ የሆነው የዱቡሻ ሥርአት ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ካለው ጉልህ ፋይዳ አንጻር የዓለም ሀብት መሆን እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ሽኩር ናቸው።


 

የዱቡሻ ሥርአትን በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርስነት ለማስመዝገብ ከተቀመጡ መስፈርቶች ሁለቱን እንደሚያሟላና ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የጥናት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ሥርአቱ ከጋሞዎች ባለፈ የዓለም ቅርስ እንዲሆን ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሀገር በቀል ዕውቀት የሆነው የዱቡሻ ሥርአት የጋሞዎች ባህላዊ የሸንጎ ሥርአት እንደሆነና በእውነት ላይ የተመሠረተ ፍርድ የሚሰጥበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ይህም አካባቢው የሰላም ተምሳሌት እንዲሆን ከማገዝ በላይ ለሀገር ሰላም እና ለህዝብ አንድነት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ተመስገን ምንዋጋው (ዶ/ር) እና ሰይድ አህመድ (ዶ/ር) የ"ዱቡሻ" ሥርአት ለህዝቦች ሰላም፣ አብሮነት፣ አንድነትና ልማትን ለማፋጠን ባለው ፋይዳ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብ ውይይት ተደርጎበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም