ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ታደርጋለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በ80ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ብሔራዊ ጥቅሞቿን እና የአፍሪካን ጥቅሞች በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኘሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ኒው ዮርክ ገብቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን ያካተተው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በኒውዮርክ 'ደህናነት በአብሮነት'' (better together) በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው ተሳትፎ ማድረግ ጀምሯል።


 

ኢትዮጵያ በጉባዔው ላይ የራሷን ብሔራዊ ጥቅሞች እና የአፍሪካን ጥቅሞች በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ንቁና ጠንካራ ተሳትፎ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከዋናው ጉባዔ በተጨማሪ በርካታ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች ላይም ኢትዮጵያ የራሷን ብሄራዊ ጥቅሞች ቅድሚያ ሰጥታ እንደምተሳተፍም አመልክተዋል።

ዓለም በተለያዩ የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች እየተፈተነች ባለበት ወቅት የሚከበረው የተመድ 80ኛ ዓመት ላይም አባል ሀገራት ከመቼውም ጊዜ በላይ አብሮነታቸውን በማጠናከር የተሻለች ዓለም ለመፍጠር መሥራት እንደሚገባቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም