የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የህብረ ብሄራዊ አንድነት መገለጫና የማንሰራራት ጅማሮ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የህብረ ብሄራዊ አንድነት መገለጫና የማንሰራራት ጅማሮ ማሳያ ነው
ሀዋሳ፤ መስከረም 12/2018(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የህብረ ብሄራዊ አንድነት መገለጫና የማንሰራራት ጅማሮ ማሳያ ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ በየነ በራሳ ተናገሩ።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን በማስመልከት የተለያዩ አካላትና የህብረተሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት የፓናል ውይይት በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ በየነ በራሳ፤ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የውጭ ጫናዎችን በመቋቋምና በርካታ መሰናክሎችን በማለፍ ለስኬት መብቃቱን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት የመንግስት ቁርጠኝነትና የላቀ የዲፕሎማሲ አካሄድ እንዲሁም የህዝቡ ተሳትፎ፣ ትብብርና ድጋፍ የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የህብረ ብሄራዊ አንድነት መገለጫና የማንሰራራት ጅማሮ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በግድቡ የግንባታ ሂደትና ስኬት የነበረንን ጽናት፣ ጠንካራ ትብብርና አብሮነት በማስቀጠል የኢትዮጵያን ወደብ መሻት ማሳካት የግድ መሆኑንም አንስተዋል።
የክልሉ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ክፍሌ ሀሜሶ፤ በመንግስት ቁርጠኝነትና በህዝቡ ያልተቆጠበ ድጋፍ ለስኬት በመብቃቱ ደስታውም የጋራችን ሆኗል ብለዋል።
በመሆኑም ከህዳሴው ግድብ ስኬት በመነሳት በቀጣይ ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በህብረ ብሄራዊ አንድነት መገንባትና ማሳካት አለብን ነው ያሉት።
የሲዳማ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ዘሪሁን ቃሚሶ፤ የግድቡ ግንባታ ሂደት የንግዱን ማህበረሰብ ጨምሮ ሁሉም በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በጥሪቱ ተሳትፎ ያደረገበት መሆኑን አንስተዋል።
የሲዳማ የሀገር ሽማግሌና የጎሳዎች መሪ ሻምበል በላይ፤ የህዳሴ ግድብ ሀብትን አልምቶ በፍትሃዊነት የመጠቀም ጥያቄ እንደነበር አስታውሰው በብዙ ልፋትና ጥረት ምላሽ በማግኘቱ ተደስተናል ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መመረቁን በማስመልከት በሲዳማ ክልል በነገው እለት ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ አንደሚካሄድ ይጠበቃል።