የሀዲያ የዘመን መለወጫ "ያሆዴ" በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የላቀ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የሀዲያ የዘመን መለወጫ "ያሆዴ" በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የላቀ ሚና አለው

ሆሳዕና፤ መስከረም 12/2018(ኢዜአ)፦ የሀዲያ የዘመን መለወጫ "ያሆዴ" በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የላቀ ሚና እንዳለው የሀዲያ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።
የሀዲያ የዘመን መለወጫ እና የአዲስ ዘመን ብስራት የሆነው "ያሆዴ"ን በማስመልከት የተዘጋጀ የባህልና ቱሪዝም የፎቶ ኤግዚቢሽን በሆሳዕና ከተማ ተከፍቷል፡፡
የፎቶ ኤግዚቢሽኑን የከፈቱት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) ናቸው፡፡
የሀዲያ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ መስፍን ቦጋለ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የሀዲያ የዘመን መለወጫ "ያሆዴ" በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የላቀ ሚና አለው ብለዋል።
የሀዲያ የዘመን መለወጫ እና የአዲስ ዘመን ብስራት የሆነው "ያሆዴ" በዓል አንዱ መገለጫ ሲሆን በአብሮነት እንደሚከበርና ዛሬ የተከፈተው የባህልና ቱሪዝም ኤግዚቢሽንም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡
"ያሆዴ" የክረምቱ ጭጋግ አልፎ ሰማዩ ሲፈካ እንደሚከበርና ይህም አዲስ ተስፋንና ልምላሜን በመያዝ የመጻኢ ጊዜን ብሩህነት በማለም እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
በዓሉ በእርቅ፣ በፍቅርና በአንድነት እንደሚከበር ጠቁመው ይህም በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የላቀ ሚና አለው ብለዋል።
በተለይ በዓሉ ያለው ለሌለው በማካፈል፣ በመደጋገፍና በአብሮነት የሚከበር መሆኑን ጠቁመው፣ ማህበራዊ መስተጋብር የማስፋትና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የያሆዴ በዓልን በማስመልከት ዛሬ የተከፈተው የፎቶ ኤግዚቢሽን የበዓሉን ባህላዊ እሴቶች አስጠብቆ በማስቀጠል ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያጠናክርም አመልክተዋል።
በፌደራልና በክልል ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች የተጎበኘው የፎቶ ኤግዚቢሽን ለሁለት ቀናት ለእይታ ክፍት እንደሚሆንም ታውቋል።