ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል - የግብርና ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል - የግብርና ባለስልጣን
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2018(ኢዜአ)፦ ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ዓለም አቀፍ መስፈርትን የጠበቁ እንዲሆኑና ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂ መዘጋጀቱን የግብርና ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን፣ የተመድ የምግብና እርሻ ድርጅት ኃላፊዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አውደ ጥናት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ እንደተናገሩት የግብርና ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ ሲላኩ ከበሽታ ነጻ መሆናቸውንና ጥራታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ ነው።
በዚህም ከዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት መመዘኛዎች አንጻር ምርቶች ከእርሻ ጀምሮ ወደ ውጭ እስከሚላኩ ባለው ደረጃ ያሉ ክፍተቶች ላይ ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም የባለሙያ እጥረት፣ የላብራቶሪ አለመሟላት፣ ለበርካታ ዓመታት የቆየና ከጊዜው ጋር ያልዘመነ የህግ ማዕቀፍና የቴክኖሎጂ ክፍተቶች መለየታቸውን አብራርተዋል።
እነዚህን ክፍተቶች ማሟላት የሚያስችል የአምስት ዓመት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ወደ ትግበራ ይገባል ብለዋል።
የአበባ ምርቶች ከእርሻ ጀምሮ እስከ ውጭ ገበያ ድረስ ከተባይ ነጻ በሆነ አግባብ ለማምረትና ለገበያ ተደራሽ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መዘጋጀቱንም አንስተዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ(ዶ/ር) ስትራቴጂው ወደ ውጭ የሚላኩና ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶች በአህጉርና ዓለም አቀፍ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በተመድ የምግብና እርሻ ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ኃላፊ ፋራዪ ዚሙድዚ፥ በበኩላቸው በጋራ የተዘጋጀው ስትራቴጂ በውጤታማነት እንዲተገበር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የእጽዋት ደህንነት ጥበቃ በደንብ እንዲጠናከርና ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ በዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ እንድትሳተፍ በጋራ እንሰራለን ነው ያሉት።